top of page

አቶ ጌታቸው ረዳ በወልቃይት-ጠገዴ-ሰቲት ሁመራ ዞን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች ካልሰፈሩ ሕወሃት ጥቃት እንደሚሰነዘር አስጠነቀቁ 

  • Writer: AAA-admin
    AAA-admin
  • 45 minutes ago
  • 1 min read

ማስታወቂያ፡- የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ከግጭት፣ ከጥቃት እና ከፖለቲካ ጭቆና ጋር የተያያዙ  የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን የሚመዘግብ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ መንስታዊ ያልሆነ  ድርጅት ነው። የማኅበሩ አንዱ አንኳር ተግባር ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ተመራማሪዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ መረጃ ማሳወቅ ነው።ማኅበሩ በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሠረቱ ማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶችን አይደግፍም።


ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. (June 25, 2025) 


ሰኔ 16 ቀን በብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት እና በወልቃይት-ጠገዴ-ሰቲት ሁመራ ዞን (ወልቃይት ዞን) ተወካዮች መካከል በሰቲት ሁመራ ከተማ ስብሰባ ተካሄዷል። ስብሰባው ከአንድ  ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች  ከትግራይ ክልል ወደ ወልቃይት ዞን እንዲሰፍሩ በታሰበው ዕቅድ ላይ ያተኮረ ነበር።  


የብልጽና ፓርቲ ልዑካን ቡድኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ እና የትግራይ ጊዜያዊ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አረጋ ከበደ እና የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ይገኙበታል። የልዑካን ቡድኑ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እና ሌሎች የወልቃይት አስተዳደር እና የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሥራ ኅላፊዎችን አነጋግሯል።ስብሰባውን አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አረጋ ከበደ እና ይርጋ ሲሳይ በጋራ መርተውታል።    


አቶ ጌታቸው በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) በወልቃይት ዞን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው ጦርነትን ለማስቀረት የትግራይ ተወላጆችን በዞኑ ለማስፈር መስማማት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።   


ነገር ግን ኮሎኔል ደመቀ እና የዞኑ ሚሊሻ ኅላፊ ዕቅዱ ከመፈጸሙ በፊት መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አቅርበዋል። 

  1. የሚመለሱ ግለሰቦች ወልቃይት-ጠገዴ-ሰቲት ሁመራ የአማራ ክልል አካል መሆኑን አምነው ይህን የሚያረጋግጥ ሰነድ መፈረም ይኖርባቸዋል። 

  2. «ምዕራብ ትግራይ» የሚለው አጠራር በወልቃይት አስተዳደር ዕውቅና የሌለው በመሆኑ ከዚህ በኋላ ጥቅም ላይ መዋል የለበትም።   

  3. በዞኑ ይሰፍራሉ ተብሎ የተገለጸው አንድ ሚልየን የትግራይ ተወላጆች ቁጥር «የተጋነነ» እና «ፖለቲካዊ» በመሆኑ ውድቅ ተደርጎ በቁጥሩ ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት። 


የወልቃይት አስተዳደር ሃላፊዎች በማብራሪያቸው በዞኑ ለማስፈር የቀረበውን የአንድ ሚሊዮን የትግራይ ተወላጆች አሃዝ ለፖለቲካ ሲባል የተጋነነ ነው በማለት ተከራክሯል። የዞኑ ባለስልጣናት  ሰባተኛውን ሀገር አቀፍ የሕዝብ ቆጠራ በማጣቀስ፣የወልቃይት አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት በወቅቱ ወደ 350,000 አካባቢ እንደነበር እና አሁን ባለው ትንበያ ወደ 450,000 እንደሚገመት ገልጸዋል። በዚሁ መሠረት አንድ ሚሊዮን የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች የሚባለው ቁጥር ትክክል ሊሆን እንደማይችል ተከራክረው፣ ይህ የቀድሞ ሰፋሪዎች አስመስለው የትግራይ ታጣቂዎችን ለማስገባት የታሰበ እንደሆነ ገልጸዋል።   


የወልቃይት ባለስልጣናት ትሕነግ ወደ ወልቃይት እንዲሰፍሩ የሚፈልጋቸውን የቀድሞ ሰፋሪዎች ማንነት እንደሚያውቁ ገልጸዋል።በወልቃይት የአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ላይ ያልተሳተፉ እና ከትሕነግ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወዲያውኑ ሊመለሱ እንደሚችሉ ገልጸው፤ማንኛውም ተመላሽ የአከባቢውን የአማራ ማንነት ሙሉ እውቅና ሰጥቶ መሆን እንዳለበት አረጋግጠዋል። ትሕነግ በወልቃይት ዞን ላይ ጥቃት ቢፈጽም የሚከተለው ውጤት ከባድ እንደሚሆንም  አስጠንቅቀዋል።  


 
 
 

Comments


Share this  site on Twitter

  • Facebook
  • Twitter

©2021 by Amhara Association of America.

bottom of page