በአማራ ክልል እና በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በአገዛዙ አካላት እየተካሔዱ የሚገኙት የዘር ማጥፋት ጥቃቶች የፈጠሩት ስጋት
- AAA-admin

- 26 minutes ago
- 5 min read

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ
በአማራ ክልል እና በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በአገዛዙ አካላት እየተካሔዱ የሚገኙት የዘር ማጥፋት ጥቃቶች የፈጠሩት ስጋት
ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. (ሜይ 27፣ 2026)
ማጠቃለያ
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በአብይ አህመድ በሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ኃይሎች እና አጋሮቹ በአማራ ማህበረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ጥቃት መቀጠሉን በተመለከተ ያለውን ከፍተኛ ስጋት ይገልጻል። ከ2018 ዓ.ም አጋማሽ (እ.ኤ.አ. 2026 መጀመሪያ) አንስቶ የአገዛዙ አካላት ባለፉት አምስት የጦርነት ዓመታት በክልሉ ውስጥ በንፁሀን ህዝብ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ቀጥለውበታል። የጥቃቶቹ መገለጫዎች የሃይማኖት መሪዎችን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (ኢኦተቤ) ተከታዮችም ላይ ጭምር ያነጣጠሩ በመሆናቸው በሃይማኖት ነፃነት ላይ ተጨማሪ ስጋትን ፈጥሯል። እነዚህ ጥሰቶች፣ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ መደፍረስና ማኅበራዊ ቀውስ ግንቦት 2018 ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ከሚደረጉ ዝግጅቶች ጋር ጎን ለጎን እየቀጠሉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የተጠያቂነት እጦት ሁኔታ ሰላምን፣ ነፃነትንና ፍትህን ለሁሉም ለማስፈን ለሚሰሩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆን ይገባል።
በንፁሀን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና በደሎች
ከታኅሣሥ 2018 ዓ.ም አጋማሽ እስከ ግንቦት 2018 ዓ.ም አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ከ242 በላይ የሰብአዊ መብት ረገጣ ክስተቶችን (የአየር ጥቃቶችን ሳይጨምር) መዝግቧል፤ በዚህም ምክንያት 2,601 ንፁሀን ሰለባ ሆነዋል። ከሰለባዎቹ መካከል 448 ተገድለው፣ 351 ቆስለዋል፣ 12 የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎች ሆነዋል፣ 349 ታፍነዋል። እንዲሁም 1,441 ሰዎች ታስረዋል። እነዚህ ክስተቶች በአማራ ክልል እና አካባቢው በሚገኙ 110 ወረዳዎች እና 21 ዞን መስተዳድሮች ውስጥ የተፈጸሙ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ባሉ የአገዛዙ አካላት የተፈጸሙ ናቸው። በብርሃኑ ጁላ የሚመራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ዋና ዋና የአገዛዙ መዋቅራዊ ክፍሎች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ማሳየታቸውን በቀጠሉበት ወቅት በጥቃቶቹ ላይ እንደ ሰሜን ምስራቅ አማራ ባሉ አካባቢዎች የትግራይ ሠላም ኃይሎች እና በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የገዳ ኮማንዶ ኃይል ያሉ ተጨማሪ አካላት መሳተፋቸው የበደሉን መጠን አባብሶታል።
ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት በርካታ ክስተቶች ተመዝግበዋል። በግንቦት 13 ቀን የአገዛዙ ኃይሎች በኪረሙ ወረዳ ሰምቦ አካባቢ በአስር ንፁሀን ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል፤ ከሟቾቹ መካከል ሴቶች፣ ታዳጊዎች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል። በግንቦት 14 ቀን በራያ ቆቦ ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች ያለአንዳች ልዩነት የተፈጸመው የከባድ መሣሪያ ድብደባ ህፃናትን ጨምሮ ለበርካታ ንፁሀን ሞትና መቁሰል ምክንያት ሆኗል። ተጎጂዎቹም ወደ ጤና ተቋማት የመሄድ ዕድል ተከልክከዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የተጎጂዎችን የአካል ጉዳት የሚያሳዩ ምስሎች ደርሰውታል። በግንቦት 12 ቀን በንፋስ መውጫ ከተማ (ላይ ጋይንት ወረዳ) በአንዲት ወጣት ልጃገረድ ላይ በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የቡድን አስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሟል።
ማኅበሩ ከታኅሣሥ 2018 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል እና በአከባቢው ባሉ የከተማ እና የገጠር አካባቢዎች በ30 ወረዳዎች እና 13 ዞን መስተዳድሮች ውስጥ 217 ንፁሀን (117 ሞት እና 100 ጉዳት) ሰለባ የሆኑባቸው 135 የአየር ጥቃቶችን መዝግቧል። ጥቃቶቹ በተከታታይ እንደ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ አምቡላንሶች፣ የእምነት ቦታዎች፣ የመኖሪያ ቤቶች እና ሌሎችንም የህዝብ አገልግሎት ተቋማትን ዒላማ ያደረጉ ነበሩ። አብዛኛው ጊዜ የአየር ጥቃቶቹ ህዝብ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ፤ ከእነዚህም መካከል የካቲት 8 በወረታ ከተማ (ፎገራ ወረዳ)፣ የካቲት 15 በሻውራ (አለፋ ወረዳ)፣ መጋቢት 23 በመካነ ኢየሱስ (እስቴ ወረዳ)፣ መጋቢት 27 በፈረስ ቤት (ደጋ ዳሞት ወረዳ)፣ ሚያዝያ 11 በጃማ (አነደድ ወረዳ)፣ ሚያዝያ 29 በወገዳ (ስማዳ ወረዳ) እና ግንቦት 5 በማህደረ ማርያም (ፋርጣ ወረዳ) የተፈጸሙት ጥቃቶች ይጠቀሳሉ።
በራያ አካባቢ በትሕነግ (ትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር) ታጣቂዎች በተያዙ ቦታዎች ነዋሪዎች የትሕነግ ዘመን የአፓርታይድ ዓይነት አስተዳደርን የሚያስታውስ የዕለት ተዕለት በደል እና መሠረታዊ መብቶችን የመከልከል ሁኔታ እየደረሰባቸው ይገኛል። በዚህ አካባቢ ባሉ የሃይማኖት ማህበረሰቦች ላይ በተለይም በኢኦተቤ ካህናት እና ምዕመናን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቀጥለዋል። በደሎቹ በክልሉ ስለሚታየው የሃይማኖት ነፃነት ሁኔታ ከባድ ስጋት ፈጥረዋል። በተጨማሪም በቅርብ ወራት ውስጥ እንደ ትምህርት ቤቶች ያሉ የሕዝብ ተቋማት በስፋት መዘጋታቸውን ተከትሎ የታዳጊዎች እገታና የግዳጅ ውትድርና እየተካሄደ ይገኛል።
የቤተሰቦች የዘፈቀደ እስራት፣ የፖለቲካ እስረኞች እንግልት እና እገታዎች
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የአገዛዙ ኃይሎች "ከፋኖ አባላት ጋር ዝምድና አላቸው" በሚል ክስ የቤተሰብ አባላትን ያለአግባብ ማሰር ቀጥለዋል። ለአብነት ያህል በግንቦት 14 ቀን የአገዛዙ ኃይሎች በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ቦሎ ጊዮርጊስ አካባቢ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ያገቱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ወይዘሮ አለምሸት መንግስቱ፣ የ3 ዓመት ልጃቸው ዮሐናን መለሰ እና ዳግም ውቤ ይገኙበታል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአካባቢዋ የሚገኙ ታዋቂ የፖለቲካ እስረኞች መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶቻቸው በድጋሚ እንደተጣሱ እና በአካላዊ ደህንነታቸው ላይ ዛቻ እንደደረሰባቸው ተዘግቧል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በብሔራቸው እና/ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ከሦስት ዓመታት በላይ ታስረው የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው እስረኞች በድንገት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ወደ አባ ሳሙኤል እና ቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች ተዛውረዋል። ዝውውሩ እስረኞች ቀጣይነት ያለው የአካልና የቃል ስድብ እየደረሰባቸው በሚገኝበት፣ ከአደገኛ ወንጀለኞች ጋር በመቀላቀላቸው ምክንያት ደህንነት እንደሌላቸው፣ የምግብ እና የውሃ እጥረት፣ የህክምና እገዳ፣ ተገቢው መኝታ እጥረት፣ ደካማ የንጽህና ሁኔታዎች እና በቤተሰብና በሕግ አማካሪ የመጠየቅ መብት መከልከል መረጃዎች ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። በተጨማሪም እስረኞች እና ሊጠይቋቸው የሚመጡ ሰዎች በማረሚያ ቤቱ ግቢ እና አካባቢው በታጣቂዎች ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ ናቸው። ማኅበሩ በግንቦት 2 ቀን ወደ ቃሊቲ የተዛወሩ የ57 እስረኞችን ስም ደርሶታል። ከእነዚህም መካከል የተከበሩ ክርስቲያን ታደለ፣ የተከበሩ ዮሐንስ ቧያለው፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው፣ ዶ/ር ማዕረጉ ቢያበየን፣ ዶ/ር መሰረት ቀለምወርቅ፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና ሌሎችም ይገኙበታል። በተጨማሪም ከጥቂት ቀናት በኋላ ሌሎች 94 እስረኞች ወደ አባ ሳሙኤል የተዛወሩ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ መሪጌታ በላይ አዳሙ፣ ዲያቆን ገብረሚካኤል አባይ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ለእነዚህ ዝውውሮች እንደ ምክንያት የቀረበው ግንቦት 2018 ዓ.ም ከሚካሄደው ምርጫ ጋር ተያይዞ ሊነሳ ይችላል ተብሎ ከታሰበው አለመረጋጋት ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም በአገዛዙ እና መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት አማካኝነት ሀገር አቀፍ እገታዎች በስፋት ቀጥለዋል። ለምሳሌ በግንቦት 11 ቀን በወረጃርሶ ወረዳ አሊዶሮ አካባቢ መጠነ-ሰፊ የእገታ ክስተት ተመዝግቧል። ክስተቱ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ በሚጓዝ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የተፈጸመ ጥቃት ሲሆን አራት ንፁሀን ቆስለው ከ43 በላይ ሰዎችን ደግሞ ታግተዋል። ይህ ክስተት በመስመሩ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እና ለክፍያ የሚደረግ እገታ አካል ነው። ጥቃቱ በአብዛኛው በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች የሚፈጸም ሲሆን የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር የፖለቲካ እና የወታደራዊ ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት ይነገራል። ጥቃቶቹ በአብዛኛው የአማራ ተወላጅ የሆኑ መንገደኞችን በማንነታቸው መለየትን ያካትታሉ። በተለይም በአካባቢው የጸጥታ መዋቅሮች ምንም ዓይነት ትርጉም ያለው የመከላከል እርምጃ አለመወሰዱ አገዛዙ በጥቃቱ ላይ ተባባሪ ነው የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።
በምርጫ ዝግጅት ወቅት የሚፈጸም የመብት ጥሰት
በኢትዮጵያ የቀጠለው የጸጥታ ችግር በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድን የማይቻል አድርጎታል። በትግራይ የቀድሞው ክልላዊ መስተዳድር መመለሱ በክልሉ ምርጫ ይካሄዳል ወይ የሚለውን ጥርጣሬ ውስጥ የጣለ ሲሆን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለው ሁኔታ ግን አሁንም ምላሽ ያላገኘ እና በአገዛዙ በተለይም በህዝቦች መካከል ክፍፍልን ለመፍጠር ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ቁማር እና መጠቀሚያ ሆኖ ቀጥሏል። በተጨማሪም ፖለቲካዊ ተቃውሞን አለመቀበል እና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት ላይ የተጣለው ከባድ ገደብ ለእውነተኛ የምርጫ ሒደት አስፈላጊ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ አካላትን ያዳክማሉ። ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆነው ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ያለው መጠነ ሰፊ የማንነት ማጣራት (profiling) እና የዘፈቀደ እስራት ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ የፓርላማ አባላት፣ ገለልተኛ የሜዲያ ሠራተኞች፣ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ሌሎችም በከባድ ሁኔታዎች ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ። የጭቆና መገለጫዎቹ በሀገሪቱ ዋና ከተማ በአዲስ አበባም ቀጥለዋል። ለምሳሌ ባለፈው ወር በአርቲስት ቴዲ አፍሮ “ኢቶሪካ” የተሰኘው አዲስ አልበም መለቀቁን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በአገዛዙ ኃይሎች ትንኮሳ እና እስራት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል።
በዚህ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ አገዛዙ በኃይል፣ በማስገደድ፣ በዝርፊያ እና በሌሎች ሕገ ወጥ መንገዶች መጠነ ሰፊ የምርጫ ዝግጅቱን ቀጥሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዜጎች የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ እና ለገዥው ፓርቲ ድምጽ እንዲሰጡ ለማስገደድ መጠነ ሰፊ ዛቻዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ ስቃይ፣ ከሥራ ማባረር እና ከመጠን በላይ የገንዘብ ቅጣቶች እየተጣሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለቀጠለው መጠነ ሰፊ በደል እና ከምርጫ ጋር ለተያያዘው የማስገደድ ድርጊት ምላሽ ለመስጠት በኢትዮጵያ ውስጥ እና ውጭ የተቃውሞ ሰልፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በመጋቢት 2018 ዓ.ም በአማራ ክልል በሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞዎች የተመዘገቡ ሲሆን ህዝቡ እየደረሰ ያለውን በደል እና የምርጫ ሂደቱን አውግዟል። በተመሳሳይ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በአውስትራሊያ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የዓለም አቀፉ ዳያስፖራ አባላት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂደዋል።
ምክረ-ሃሳቦች
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉትን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች በጋራ እንዲያወግዙ፤ በተለይም በአገዛዙ እና አጋር ቡድኖች ላይ ቀጥተኛ ውግዘት እንዲያቀርቡ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም ማኅበሩ የዓለም አቀፍ አጋር ሀገራት እና የገንዘብ ተቋማት ተጨማሪ በደሎችን ለመፈጸም የሚያገለግሉ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የሚውሉ ማናቸውንም የገንዘብ ድጋፎችን ማድረግ እንዲያቆሙ እና በጥቃቶቹ ላይ እጃቸው ያለባቸውን ባለስልጣናት እና ወታደራዊ መሪዎችን ዒላማ ያደረጉ ማዕቀቦችን እንዲጥሉ ጥሪ ያደርጋል።












Comments