በአማራ ክልል እና በአቅራቢያው በሚገኙ አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣው የሠላም እጦት ስጋት
- AAA-admin
- 6 hours ago
- 5 min read

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ
ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም. (ፌብሩወሪ 8፣ 2026)
አጠቃላይ ዕይታ
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ከታኅሣሥ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል እና በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ካለው የዘር ማጥፋት ጦርነት ጋር በተያያዘ ተባብሶ የቀጠለው ግፍና ጭካኔ ስጋት ላይ እንደጣለው ይገልጻል። ይህ መባባስ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ሥርዓት ባለፉት ሦስት ዓመታት ባካሄደው ጦርነት የተመዘገቡ የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቀጣይ ሲሆን የጦርነቱም ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ የክልል አጋሮችን ያካትታል። ጥቃቶቹ በዋናነት የአማራ ማንነትን እና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (ኢኦተቤ) ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው።
በንፁሀን ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በአማራ ክልል በራያ ቆቦ፣ ቡግና፣ ወግዲ፣ ጃቢ ጠህናን፣ ደምበጫ፣ አዮ ጓጉሳ፣ ደቡብ ሜጫ፣ ጎንጂ ቆለላ፣ ጉና በጌምድር እና ጠለምት ወረዳዎች በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ሰሜን ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎችን መዝግቧል። በጠለምት የተፈጸመው ጥቃት በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ኃይሎች ሲሆን የተቀሩት ጥቃቶች በሙሉ የተፈጸሙት በኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ኃይሎች ነው። በወግዲ በቅርቡ በጄኔራል አድማሱ አለሙ እና በዘውዱ ሰጥአርጌ በሚመሩ የአገዛዙ ኃይሎች በተፈጸሙ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ያነጣጠሩ የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች በሠላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ከ113 በላይ ንፁሀን ዜጎች ሕይወት ማለፉን እና ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች እንደቆሰሉ ይገመታል። በኤፍራታና ግድም ጥቃት በአማራ ክልል ከሚገኘው አጎራባች «የኦሮሞ ልዩ ዞን» ተሻግረው በመጡ የአገዛዙ ኃይሎች የሚታገዙ የኦሮሞ ታጣቂዎች የተፈጸመ ነው። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳም እንዲሁ አንድ የጅምላ ግድያ በጉሙዝ ታጣቂዎች መፈጸሙ ተነግሯል።
በተጨማሪም የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች በሲቡ ሲሬ እና በደራ ወረዳዎች የጅምላ ግድያዎችን መዝግቧል። እነዚህ ጥቃቶች በኦሮሞ ልዩ ኮማንዶ (ገዳ ኮማንዶ) ኃይል እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ታጣቂዎችን እንደተፈጸሙ ተመላክቷል።
የጅምላ እስር እና አፈና
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በአላማጣ ከተማ፣ ኦፍላ፣ ላሊበላ ከተማ፣ መቄት፣ ሀብሩ፣ አምባሰል፣ ወግዲ፣ ኮምቦልቻ ከተማ፣ ኢፍራታና ግድም፣ ደብረ ማርቆስ ከተማ፣ ጃቢ ጠህናን፣ ደምበጫ፣ ወምበርማ፣ አዮ ጓጉሳ፣ ሰሜን ሜጫ፣ ባህርዳር ከተማ አውራጃዎች በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም እና ባህርዳር ከተማ ዞኖች በመቶዎች በሚቆጠሩ ሠላማዊ ዜጎች ላይ እስራትና አፈና መፈጸሙን ዘግቧል። በአላማጣ ከተማ እና በኦፍላ አውራጃ በትሕነግ ኃይሎች ከተፈጸሙት እስራቶችና አፈናዎች በስተቀር የተቀሩት በሙሉ የተፈጸሙት በኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ኃይሎች ነው።
የክልል የጸጥታ ኃይሎች የሚፈጽሙት የጅምላ እስር አብዛኛው ጊዜ ከጦር ሜዳ ሽንፈት ጋር የተያያዘ ሲሆን ሰለባዎቹ ለግዳጅ ውትድርና ወደ ወታደራዊ ተቋማት የሚወሰዱ ሲሆን አንዳንዶቹም ለጦርነት ፕሮፓጋንዳ (ታሳሪዎችን በመንግስት መገናኛ ብዙኃን እንደ ምርኮኞች ለማቅረብ) ይውላሉ። በራያ አካባቢም እንዲሁ የትሕነግ ኃይሎች የግዳጅ ውትድርና ይፈጽማሉ።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ በሚገኙ ደራ እና ወረ ጃርሶ ወረዳዎች እንዲሁም በጅማና በምሥራቅ አርሲ ዞኖች በሚገኙ ገራ እና ሆንቆሎ ወረዳዎች እገታዎች ተፈጽመዋል። እነዚህ እገታዎች የኦነሰ ታጣቂዎች እና ያልታወቁ ታጣቂዎች እንደፈጸሙት ይመላከታል። ይህም የአማራ ብሔር እና የኢኦተቤ አማኞች ላይ ያነጣጠረ የቀጣለው ዘመቻ አካል መሆኑ ያሳያል።
የሀገር ውስጥ መፈናቀል ቀውስ
በጥር 2018 አጋማሽ የትሕነግ ኃይሎች በሰሜን ምስራቅ አማራ አካባቢዎች ወረራ በማድረግ ለነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌዴራል ኮማንድ ፖስቱ ከቦታው እንዲወጣ ተደርጓል። መፈናቀሉ በአላማጣ ከተማ፣ በራያ አላማጣ፣ በራያ ባላ፣ በኮረም ከተማ እና በኦፍላ ወረዳዎች (እና አካባቢው) የተከሰተ ሲሆን ይህም ቆቦ ከተማን ጨምሮ በአጎራባች የከተማ ማዕከላት ውስጥ ከፍተኛ የውስጥ ተፈናቃዮችን አስከትሏል። መፈናቀሉ የተከሰተው የትሕነግ ኃይሎች እና የትግራይ ሰፋሪ አስተዳደር ለወራት በነዋሪዎች እና ከኢኦተቤ ጋር ግንኙነት ባላቸው የሃይማኖት አባቶች ላይ ሲፈጽሙት የነበሩት ጥቃቶች፣ እስሮች፣ አፈናዎች እና ትንኮሳዎች በቀጠሉበት ነው።
ይህ ክስተት ከአጎራባች ኦሮሚያ ክልል እና አካባቢው በዘር ማጥፋት ጦርነት፣ በጥቃት እና በስደት ምክንያት ተፈናቅለው በአካባቢው በሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ምክንያት የተፈጠረውን ቀውስ አባብሶታል። በተጨማሪም የሰብአዊ ድርጅቶች የሚደረግ ድጋፍ እጦት የሰብአዊ ቀውሱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል። ይህም የበለጠ ሰዎች ከተፈናቀሉ እንደሚባባስ ይጠበቃል።
የግንኙነት ዳግም መቋረጥ
በተገኘው መረጃ መሠረት በአማራ ክልል እና በአካባቢው ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የበየነ መረብ ግንኙነት መቋረጥ ተስተውሏል። የግንኙነቱ መቋረጥ የተጀመረው ጥር 25 ቀን 2018 በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በአዊ፣ በማዕከላዊ ጎንደር እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች እና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች ሰሜን ሸዋ ዞን ሲሆን ከመስመር ስልኮች በስተቀር የሞባይል፣ የበየነ መረብ እና ሌሎች አገልግሎቶች በሙሉ ተቋርጠዋል። መቋረጡ ያጋጠማቸው ወረዳዎች በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ እና ጃማ ወረዳዎች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት፣ አንኮበር፣ መንዝ ማማ ምድር፣ ጣርማበር፣ መርሃቤቴ እና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች፤ የምስራቅ ጎጃም ዞን እናርጅ እናውጋ፣ እነማይ፣ ሸበል በረንታ፣ እንበሴ ሳር ምድር፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ፣ ቢቡንግ እና ደጀን ወረዳዎች፤ የአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ፤ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ፣ ምዕራብ ደንቢያ እና አለፋ ወረዳዎች፤ እና የምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ናቸው። ይህ የግንኙነት መስተጓጎል የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ኃይሎች እያደረጉ ካለው ክልል አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ እና በንፁሀን ላይ እየፈጸሙት ከሚገኘው ጥቃት ጋር የተያያዘ ነው። መስተጓጎሉ የመረጃ ፍሰትን በእጅጉ ገድቧል፤ ግንኙነት አቋርጧል፤ እንዲሁም እየተባባሰ በመጣው የወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት የሚያስፈልጉ የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶችን እና ገለልተኛ መረጃ ማግኘትን አስቸጋሪ አድርጎታል። በተገኘው መረጃ ከበርካታ ቀናት በኋላ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች አገልግሎቶቹ የተመለሱ ቢሆንም መቋረጡ እንደገና ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለ። በተለይም በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ተፈጥረው የነበሩት የግንኙነት ገደቦች በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ንፁሀንን መጠበቅ፣ የሰብአዊ መብቶችን ማክበር እና ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም
አብዛኛዎቹ ጥቃቶች ተፈጸሙት በሥርዓቱ ኃይሎች ከክልል አቻዎቻቸው፣ በትሕነግ እና በኦነሰ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር ነው። ተጎጂዎቹ በአብዛኛው የአማራ ብሔር አባላት ሲሆኑ ጥቃቶች የተፈጸሙት (በተለይም የፌዴራል/ ክልል የጸጥታ ኃይሎችን የሚመለከቱ ጥቃቶች) ተጎጂዎቹ የፋኖ ተዋጊዎች ናቸው በሚል ሰበብ ነው። እነዚህ ጥቃቶች የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓይነት መልክ ያላቸው ሲሆን የሚመለከታቸው ሁሉ ለንፁሀን ጥበቃ እና የሰብአዊ መብቶች መከበርን እንዲያበረታቱ ይጠየቃል።
የፌዴራል ኃይሎች የራያ አካባቢ ነዋሪዎችን ከዳግመኛ ጥቃት መጠበቅ ያለመቻል ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ትሕነግ በቅርቡ በራያ፣ ጠለምት እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢዎች ላይ ባደረገው ወረራ ምክንያት ለተፈጠረው የተፈናቃዮች ቀውስ ፈጣን የሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት፣ በተጎዱ አካባቢዎች መረጋጋት ለመፍጠር እና ተፈናቃዮችን ዳግም ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሁሉንም ተሳትፎን ይጠይቃል። በአጠቃላይ የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ በራያ፣ ጠለምትና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ የአማራ ድንበር እና ማንነትን የማስከበርን ውሳኔ ለፖለቲካ ዓላማ ለማዘግየት የሚደረገው ሙከራ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን እንዳይመጣ እንቅፋት እየሆነ ነው። ጥር 22 ቀን 2028 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ የድምጽ መስጫ ወረዳዎችን በትግራይ ክልል አስተዳደር ሥር በማስቀመጥ የሰጠው መግለጫ አንድ ምሳሌ ነው። ይህም በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙትን የአማራ ተወላጆች የፖለቲካ ታጋቾች በማድረግ የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ የስርዓቱን የኦሮሞ ብሔርተኛ የበላይነት አጀንዳ ለማራመድ የሚያደርገውን ከፋፋይ እና ተንኮል የተሞላበት ፖለቲካ ያንፀባርቃሉ።
ይህ ታይቶ የማይታወቅ የዓመፅ መባባስ በክልል እና በወታደራዊ ባለስልጣናት፣ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን እና በመንግስት በተደራጁ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስቻይነት ቀጥሏል። በተለይም በዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሚመራው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዝምታውን በመቀጠል በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላየ የሚደረጉትን ዘገባዎች በሙሉ አቁሟል። ይህ ሁኔታ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በደሎችና ግፎች በማን አለብኝነት መፈጸም መቀጠላቸውን ያሳያል።
ምክረ ሃሳብ
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሱ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማውገዝ እንዲተባበሩ ጥሪ ማቅረቡን ይቀጥላል። ይህም የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝን እና ተባባሪ የክልል ታጣቂ ቡድኖችን በቀጥታ ማውገዝን ያካትታል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ አጋር ሀገራት እና የገንዘብ ተቋማት ተጨማሪ የመብት ጥሰቶችን ለመፈጸም የሚያገለግሉ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ለመግዛት የሚውል ማንኛውንም የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቆሙ እና ባለስልጣናት እና ወታደራዊ መሪዎች ላይ ዒላማ ያደረጉ ማዕቀቦችን በመጣል የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲከላከሉ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ጥሪ ያቀርባል።










