top of page

ፕሬዜዳንት ትራንፕ ሰለ ህዳሴ ግድብ የፃፉት ደብዳቤ ብሄራዊ ፕሮጀክቶችን ለጠባብ የፓለቲካ ግብ የሚጠቀመው የኦሮሞ ብልጽግና ሀገሪቱን በዲፕሎማሲ ዉራ እንዳደረጋት ማሳያ ነዉ።

  • Writer: AAA-admin
    AAA-admin
  • 8 hours ago
  • 2 min read

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ

ጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም. (ጃንዩወሪ 26፣ 2026)


የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ ለግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤልሲሲ ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ለተነሳው አለመግባባት ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት አሜሪካ ለማደራደር ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ልብ ብሏል።


ማኅበራችን በተደጋጋሚ እንደገለጸው በአብይ አህመድ በሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ኢትዮጵያን የትርምስ ቀጠና፣ የዘር ማጥፋት ጦርነቶች ማዕከል፣ የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያምሳት እና ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን ለፓርቲው ልሂቃን ጠባብ አጀንዳ ፖለቲካዊ ዓላማ የሚጠቀምባት የግዛት ሉዓላዊነት የሌላት በበርካታ ቡድኖች ተከፋፍለው የሚያስተዳድሩት በዲፕሎማሲ የወደቀች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል። የአብይ አገዛዝ በሃገር ዉስጥ ያጣዉን ተቀባይነት ለማካካስ ሀገሪቱ የውጭ ሃይሎች የጦር መሳሪያ እሰከሰጡት ድረሰ እንደፈለጉ የሚያዝቧት ክብር የተነሳት እና ተላላኪ ሃገር አድርጓታል።


የአባይ ወንዝ ከርሰቱ የሚፈለቀው እና ግድቡ በርስቱ መተከል ውስጥ የተገነባዉ የአማራ ህዝብ በገንዘብ መዋጮ እና ሕዝብን በማንቀሳቀስ ለግድቡ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በግንባታ ሂደቱም የመነሻ ሃሳቡን ከወጠኑት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እሰከ በግድቡ ግንባታ ሂደት በሴራ የተገደለዉ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የአማራ ሃይሎች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ያም ሆኖ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የብዙ ኢትዮጵያውያን ትውልዶች ቅብብል፣ ምኞትና ቁርጠኝነት ነጸብራቅ የሆነ እና ዲያሰፖራውን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የገንዘብ መዋጮ የተደረገለት እና የሚደገፍ ብሔራዊ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት መሆኑን በአፅንዖት ያምናል።


ሆኖም በኦሮሞ ብልጽግና ልሂቃን ግድቡን ለጠባብ የጎሳ ተኮር ፖለቲካዊ ዓላማዎች እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙበት ይገኛል።


ለዚሁ ፕሮጀክት ሲባል ለግል ጥቅማቸው የአማራን ትግል ለገዥ ገበያ መታየነት ከተጠቀሙ በሗላ ዓላማዉን የከዱ ግለሰቦች የግድብን አጀንዳ የአማራን ጥያቄዎች መሠረት የለሽ በማስመሰል በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማስቀጠያነት ሊጠቀሙበት እየሰሩ ይገኛሉ። ሆኖም አምባገነኑ የአቢይ አገዛዝ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በሚደረጉ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ዲፕሎማሲ ረገድ ያደረሰዉን ከፍተኛ ክስረት ሊደብቁለት አይችሉም። አገዛዙ አካታች አመራርን ከማስፈን ይልቅ የኦሮሞን የፖለቲካ የበላይነትን በማስቀደም በውስጥ ያልተረጋጋች በውጪ የተገለለች ኢትዮጵያን ከመፍጠር ባሻገር ከጎረቤት ሃገራት ጋር የሚያደረገው ወጥነት የሌለው እና ትንኮሳ የተሞላበት ግንኙነት በጎረቤት አገሮች መሐል አለመተማመንን በመፍጠር ሀገሪቱ የቀጠናው የአለመረጋጋት ምንጭ እንድትሆን አድርጓታል። በተጨማሪም አገዛዙ ግድቡን በስልጣን ላይ ለመቆየት መስዋዕት ሊያደርግ እንደሚችልም ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም የአቢይ አገዛዝ በግድቡም ሆነ በማንኛውም አንኳር የውጭ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ወይም ኢትዮጵያን ለመወከል ሕጋዊነት፣ ሥልጣን ወይም የሞራል አቋም የለውም።


የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በግድቡ ዙሪያ ለሚነሳ አለመግባባት ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እና ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን ተሰሚነት ወደ ቀድሞው መመለስ የሚቻለው ሕጋዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ተጠያቂነት ባለው መንግስት ሥር ብቻ እንደሆነ በጽኑ ያምናል። ፍትህ፣ ተጠያቂነት እና መረጋጋት ተዓማኚነት ላለው ዲፕሎማሲ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። አሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአብይ አገዛዝ ከአሁን በኋላ በግድቡ ወይም በሰፊው ቀጠናዊ ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ህጋዊ ተደራዳሪ መሆን እንደማይችል እንዲገነዘቡ፤ አገዛዙ በአማራ ላይ የሚያካሂደውን የዘር ማጥፋት ጦርነት እንዲያቆም እንዲደግፉ እና ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር፣ ብሔራዊ አንድነትን የሚያድስ እና ቀጠናዊ ሠላምን እና የኢትዮጵያን እና የአጋሮቿን የረጅም ጊዜ ጥቅም የሚያስጠብቅ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሽግግር እንዲደረግ ግፊት እንዲያደርጉ ማኅበሩ ጥሪ ያቀርባል።


በመጨረሻም የአማራ ትግል ወደ አንድ ውህድ ብሔራዊ ንቅናቄ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት ሁሉም አማራ የአማራ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማስቆም እና ተጠያቂ የሆኑትን ወንጀለኞች ለፍርድ ለማቅረብ እየተደረገ ያለውን ተጋድሎ መደገፍ ላይ እንዲያተኩር ማህበራችን ያሳስባል።




 
 
 

Comments


Share this  site on Twitter

  • Facebook
  • Twitter

©2021 by Amhara Association of America.

bottom of page