የአማራ ማህበር በአሜሪካ ህዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች ንፁሀን ላይ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እያደረሰ ያለው አደጋ እና እየተጠቀመ ያለው ያልተመጣጠነ ኃይል ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረበት ይገልጻል
- AAA-admin
- 8 minutes ago
- 1 min read
መግለጫ - የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. (ፌብሩወሪ 11፣ 2026)

የአማራ ማህበር በአሜሪካ በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል እና በአጎራባች አካባቢው በአማራ ህዝብ ላይ በሚያደርገው የዘር ማጥፋት ጦርነት ህዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች ንፁሀን ላይ እያደረሰ ያለው አደጋ እና እየተጠቀመ ያለው ያልተመጣጠነ ኃይል ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረበት ይገልጻል።
ከየካቲት 4 ቀን ጠዋት ጀምሮ የደቡብ ጎንደር ዞን የአስተዳደር ማዕከል በሆነችው በደብረ ታቦር ከተማ መሐል እና በመኖሪያ ሰፈሮች ላይ የአገዛዙ ኃይሎች (በተለይም የመከላከያ ሠራዊት) የአየር ድብደባ እና ከባድ መሣሪያ መተኮሳቸውን የአማራ ማህበር በአሜሪካ መረጃዎች ደርሰውታል። በአሁኑ ወቅት ባለው መረጃ መሠረት በወባባ (ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አቅራቢያ)፣ በወይበላ ማርያም፣ በአየር ማረፊያ፣ በርብ ወንዝ፣ በቄራ ኡራኤል ቤተክርስቲያን እና በወርቅን ቀበሌ አቅራቢያ የአየር ድብደባዎች እንደደረሱ መረጃዎችዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እነዚህ ጥቃቶች በንፁሀን ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተሉ ሲሆን በመኖሪያ ቤቶች እና በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ላይም ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል። ነገር ግን በቀጠለው የበየነ መረብ መገናኛ መስተጓጎል ምክንያት የደረሰው ሞትና የንብረት ኪሳራ ትክክለኛ መጠን ሊረጋገጥ አልቻለም። በተጨማሪም የፋኖ ደጋፊዎች ናችሁ በሚል ሰበብ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ሰፊ እስር እየተፈጸመ እንዳለ የአማራ ማህበር በአሜሪካ መረጃዎች ደርሰውታል።
የአማራ ማህበር በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች አገዛዙ እየተጠቀመ ያለውን የንፁሀንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ያልተመጣጠነ ኃይል እንዲያወግዙ፤ አገዛዙ እያደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያቆም፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲያከብር፣ ያለአግባብ የታሰሩ ግለሰቦች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና የበየነ መረብ መገናኛ ወደ ነበረበት እንዲመልስ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል።










