የአገዛዙ የዘር ማጥፋት ጦርነት በቀጠለበት ኢጋድ እና የአፍሪካ ኅብረት በአብይ አገዛዝ የተፈበረከውን «የሠላም ስምምነት» ሕጋዊ የማስመሰል ሂደት የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ያወግዛል
- AAA-admin
- a few seconds ago
- 2 min read

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ
ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. (ዲሴምበር 4፣ 2025)
የአገዛዙ የዘር ማጥፋት ጦርነት በቀጠለበት ኢጋድ እና የአፍሪካ ኅብረት በአብይ አገዛዝ የተፈበረከውን «የሠላም ስምምነት» ሕጋዊ የማስመሰል ሂደት የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ያወግዛል
በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ በኢትዮጵያ የአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት እያካሔደ ባለበት በዚህ ወቅት ቁልፍ አካባቢያዊ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት የያዙት ትክክለኛ ያልሆነ አቋም የአማራ ማኅበር በአሜሪካን በእጅጉ አሳስቦታል።
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በሚያደርገው የሰብአዊ መብት ክትትልና ምዝገባ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ ቁልፍ ለውጦችን በየጊዜው ይከታተላል። ባለፉት አምስት ዓመታት ጦርነት በሀገሪቱ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ እያባባሰው ቀጥሏል። የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ጥቂት ታጋዮችን እጅ መስጠት እንደ «የሰላም ስምምነት» ለማቅረብ በሚሞክርበት ወቅት የኢጋድ ሴክሬታሪያት እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የያዙትን የተዛባ አቋም በቀጠናው ካለው ቀውስ አሳሳቢነት የተነሳ ማኅበሩ ለመጠቆም ይገደዳል።
የኢጋድ የሰሞኑ አካሄድ የድርጅቱ አመራሮች የገዢውን የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ጠባብ የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈጸም ይሰራል ተብሎ ከዚህ ቀደም የሚጠረጠረውን ጉዳይ የሚያረጋግጥ ነው። የኢጋድ ሊቀ መንበር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ራሳቸው የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ፣ የኦሮሞ ብልጽግና አባል እና የአብይ አህመድ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን እየሰሩ የሚገኙት እንደ ገለልተኛ አካባቢያዊ መሪ ሳይሆን በአማራው ሕዝብ ላይ ጦርነት እንደከፈተው የገዥው አካል ቅጥያ ሆነው ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ እና አከባቢዎቹ ሕዝቦች በአስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ጊዜ ይህ ወገናዊነት ለእውነተኛ ድርድር የሚያስፈልገውን ገለልተኝነት ሙሉ በሙሉ ያጠፋል።
በተመሳሳይ መልኩ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ኅብረት ለብልጽግና አገዛዝ የሚያሳየውን አሳሳቢ የሆነ ከልክ ያለፈ ታዛዥነት ቀጥሏል። በቅርቡ የጥቂት ግለሰቦችን እጅ መስጠት እንደ እውነተኛ የሰላም ስምምነት አድርጎ ለማቅረብ ያደረገው እንቅስቃሴ እየተባባሰ የመጣውን የጦርነቱን መጠን፣ የከፋ ሰብአዊ ችግር እና በአማራው ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው መጠነ ሰፊ ስቃይ የሚያሳየው ቸልተኝነት ያሳያል። ይህ ድርጊት በሰላም እና መረጋጋት ተልእኮ ላይ ማፌዝ ነው። በዚህም ኅብረቱ ገለልተኛና ታማኝ ዳኝነት ይሰጣል የሚችለውን አምነት ያሳንሰዋል። በተጨማሪም እነዚህ አድሏዊ ድርጊቶች ኅብረቱ በሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ እና የእርዳታ ጥረቶች አስፈላጊ የሆነውን እምነት ያሳጣሉ።
አካባቢያዊ እና አህጉር አቀፍ አካላት የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝን መደገፍ አቁመው አገዛዙ በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ጦርነት ለማስቆም እና ይልቁንም እውነተኛ ሠላም እንዲሰፍን በመላ አገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ሁከትና የጸጥታ ችግር መዋቅራዊ መንስኤዎችን ለመፍታት ትርጉም ያለው እና ከአድሎ የፀዳ ጥረት እንዲያደርጉ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ጥሪውን ያቀርባል።










