top of page
  • Writer's pictureAAA-admin

ከአለም አቀፍ የአማራ ማህበራት የተሰጠ መግለጫ


ኅዳር 9 ቀን 2015 ዓ/ም


የኦህዴድ/ ብልጽግና እና የትህነግ የደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የኬንያ “የሠላም ስምምነት” ድብቅ ተልዕኮ።


ውድ የአማራ ሕዝብ ሆይ!


በኦህዴድ/ብልጽግና እና በትህነግ መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ የተካሄደው “የሠላም ስምምነት” ወደ ጦርነት በመሩት እና ጦርነቱ ባስከተላቸው ሁነቶች መሃል ገዝፈው የሚታዩትን፣ ለኢትዮጵያ ሠላምና ደኅንነት ወሳኝ የሆኑትን፣ የአማራውን ዋና ዋና ችግሮች ያላገናዘበ እንደነበር ተመልክተን፣ የአማራው ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ዘንድ የአማራ ማኅበራት የወከሏቸው ልዑካን በድርድሩ እንዲሳተፉ ድጋፋችንን መግለጻችን ይታወቃል።


ሆኖም ትናንት ከሳሽም ዳኛም ሆነው ባጸኑብህ “ሕገ-መንግሥታዊ” ፍርድ አሁን ለምትገኝበት የመከራ ኑሮ የዳረጉህ የዛሬዎቹ የሥልጣን ባላንጣዎች፣ አንተን አግልለው፣ ባላንጣነታቸውን ትተው፣ ሥልጣን ሊከፋፈሉ፤ ለ30 ዓመታት አቤት ብለህ ፍትሕ ያጣህባቸውን፣ በኋላም የሦስት ዙር ወረራና ጥቃት መክተህ በኃይልህ ያስመለስካቸውን የማንነት ጥያቄዎችን እና ርስቶችህን ዳግም ለትህነግ ለማስረከብ እንደገና “በሕገ-መንግሥቱ” እንድትዳኝ ተስማምተውብሃል። ይህን በብአዴን አጋፋሪነት ኦህዴድ/ብልጽግና እና ትህነግ የፈረዱብህን መቀበል ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ የፋኖ፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሽያ ጀግኖችህን መስዋዕትነት ከንቱ ማስቀረት ይሆናል።


ነገዳዊው ሥርዓት በህልውናህ ላይ የጋረጠውን አደጋ ከስረ-መሰረቱ ለማስወገድ የምታካሂደውን ዘላቂ ትግል ለውጤት የምታበቃው በታላቅ መስዋዕትነት ያገኘሃቸውን ድሎች በመጠበቅ፣ ኃይልህን በማጠናከር እና ቀጣይ ድሎችን በመቀዳጀት ነው። ለዚህም በመላው አለም ያሉ የአማራ ማኅበራት እና ህዝባዊ ድርጅቶች የመፍትሄ ትግሉ አካል በመሆናቸው ትግሉ በስፋት እና በጥልቀት መቀጠል እንዳለበት በጽኑ ያምናሉ። በትግልህ ያስመለስካቸው የወልቃይት፣ የጠለምት እና የራያ ርስቶችህን “በሰላም ስምምነት” ስም ከእጅህ እንዳይወጡ በየትኛውም ደረጃ በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ቁርጥ አቋምህን ማሳወቅ አለብህ። ወልቃይት፣ ጠለምት እና ራያ ዳግም ከእጅህ ነጥቀው የአማራን ግዛት ወደ ትግራይ ሊያካልሉ በኦህዴድ/ብልጽግና ደጋሽነት በብአዴን አጋፋሪነት ሽር ጉድ የሚሉለትን “ህዝበ ውሳኔ” ፍጹም መቃዎም አለብህ።


ለፋኖ፣ እንዲሁም ለአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሽያ፦


በደም እና በአጥንትህ የመለሰካቸው ርስቶችህን ዳግም እንዳትነጠቅ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ንቃት እና ብቃት ለመስዋዕትነት ዝግጁ በመሆን እንደምትጠብቅ ፍጹም እርግጠኞች ነን። በውስጥህ ያሉ ባንዳዎች እና ጠላቶቻችን ሊከፋፍሉህ፣ ሊያዳክሙህ እና ሊያጠቁህ በሰላም ሰም ተማምለው ዳግም ግምባር ፈጥረዋል። ለአማራ ህዝብህ የመከራው መጠን እና ጊዜ በማሳጠር ለዘላቂ ድል፣ ለህልውናው ባስተማማኝነት መቀጠል እና አንገቱን ቀና አድርጎ የሚኖርበት ሀገር ባለቤት ለማድረግ የገባህውን ቃል አጽንተህ መቀጠል ይኖርብሀል።


ለአማራ ወጣቶች፦


ትናንት በአያት በአባቶችህ ተገንብታ እና ተጠብቃ የቆየችውን አገርህን፣ ርስትህን፣ ቀዬህን፣ ነጻነትህን እና ህልውናህን ማስቀጠል እንሆ ያንተ አደራ ነው። ኦህዴድ/ብልጽግና እና ትህነግ ወጣትነትህን በአግባቡ በትምህርት፣ በክህሎት እና መዝናናት እንዳታሳልፍ ከትምህርት ገበታ ስትፈናቀል፣ በርስትህ እና በቀዬህ ስትገደል፣ ስትታሰር፣ ወጣትነትህን በሰቆቃ እንድታሳልፍ ፈርደውብሃል፣ ፍርዱንም ለማስፈጸም ዳግም መጥተዋል። ጊዜው ያንተ ነው! ጠላቶችህን በሁሉተናዊ ትግል ልትፋለማቸው፣ ልታቆማቸው ይገባል። ዘላቂ እና ሙሉ ህልውናህን፣ ነጻነትህን እና ሰላምህን ማስጠበቅ ያንተው ሀላፊነት ነው።


ለአማራ ምሁራን እና ልሂቃን፦


ያሳደገ፣ ያስተማረ እና ለቁምነገር ያበቃህን ወገንህን የምትታደግበት፣ ውለታውን የምትከፍለበት እና መከታ የምትሆንበት ፈታኙ ወቅት ላይ ደርሰሃል። ህዝብህ በቁርጠኛት ተነስቶ መሪውን፣ አስተማሪውን እየጠበቀ ነው። ዛሬ የገጠመውን የህልውና ፈተና ለማለፍ በታማኝነት፣ ቁርጠኝነት እና በልበሙሉነት ታነቃው፣ ታደረጃው እና ታስታጥቀው ዘንድ አሁንም ይጣራል። በብአዴናዊነት በሽታ ሳትለከፍ፣ ለግል ጥቅም እና ምቾት ሳታጎበድድ እና ሳታመነታ ከህዝብህ ጎን ቁም።


ከኢትዮጵያ ውጭ ላላችሁ አማራዎች፦


ህዝባችን በተከታታይ ገዥዎች ስር ለግማሽ ምዕተ አመት በማንነቱ በሰቆቃ ይገኛል። ሆኖም ግፍ በቃኝ በማለት ትግሉን እያፋፋመ፣ ርስቱን እያስመለሰ፣ ህልውናውን እያሰጠበቀ ለቀጣይ ትግልም እየተዘጋጀ ነው። ለዚህም ቀጣይ ትግል እኛም ከጎኑ መቆም፣ በተላይም በውጭ የሚሰሩ ስራዎችን ሙሉ በሙሉ መሸፈን፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ አቅርቦት ማደረግ፣ እንዲሁም አፋኙ ገዥ መንግስት በህዝባችን እና በመሪዎቹ ላይ የሚፈጥረውን ወከባ ለመቀነስ በመደራጀት የመሪነት ክፍተቱን ልንሸፍን ይገባል። ይህም ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ በየአካባቢያችን በሚገኙ የአማራ ድርጅቶች በንቃት በመሳተፍ ትግሉን እንቀላቀል። የህልውና ትግሉን መደገፍ እና መምራት የኛ ድርሻ ነው።


ለከፋፋዮች አትመች፤ አንድነትህን አጽና!

በሴራና በአሻጥር እንዳትጠለፍ አስተውል!

ወቅታዊ ሁነቶችን በንቃት ተከታተል!

ሕዝባዊ ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው ጥሪዎች ዝግጁ ሁን!


አለም አቀፍ የአማራ ማህበራት


ፈራሚ ማህበራት:-


1. የአማራ ማህበር በስዊዘርላንድ

2. የአማራ ማህበር በኩዊንስላንድ አውስትራሊያ

3. የአማራ ማህበር በኒው ሳውዝ ዌልስ አውስትራሊያ

4. የአማራ ማህበር በአሜሪካ

5. የአማራ ማህበር በካሊፎርኒያ (ሳንዲያጎ)

6. የአማራ ማህበር በኮሎራዶ

7. የጆርጂያ የአማራ ማህበር

8. የሎስ አንጀለስ የአማራ ማህበር

9. የአማራ ማህበር በኔቫዳ

10. የአማራ ማህበር በሲያትል

11. የዌሊንግተን ኢንኮርፖሬትድ የአማራ ቤተሰቦች ማህበር

12. የሜኒሶታ የአማራ ቅርስ ማህበር

13. የአማራ ሰብአዊ መብት እና የዘር ማጥፋት ማስጠንቀቂያ

14. የአማራ ህዝብ ሲቪክ ድርጅት ዳላስ ቴክሳስ

15. የአማራ ባለሙያዎች ህብረት

16. የአማራ ተማሪዎች ማህበር

17. የአማራ ወጣቶች ማህበር

18. የአማራ ማህበር በፈርንሳይ

19. ካልጋሪ የአማራ ማህበር

20. የካናዳ የአማራ ማህበረሰብ ህብረት

21. ደጀን ለአማራ ህልውና

22. ኤድመንተን የአማራ ማህበር

23. በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የአማራ ማህበራት ፌዴሬሽን

24. በአውስትራሊያ የአማራ ማህበራት ፌዴሬሽን

25. የዘር ማጥፋት መከላከል በኢትዮጵያ

26. የለንደን ኦንታሪዮ የአማራ ማህበር መድረክ

27. የአማራ ማህበር በኒው ኢንግላንድ

28. የአማራ ማህበር በጀርመን

29. የአማራ እና የአማራ ቤተሰቦች ኢትዮጵያዊያን ማህበር በአክላንድ ( ኒውዝላንድ)

30. በአማራ ህብረት ሙኒክ (ጀርመን)

31. የአማራ ጀግኖች አደራ ( ዩኬ )

32. የዋሽንግተን እና አካባቢው የአማራ ማህበር

33. የአማራ ድጋፍ ተራድዖና መልሶ ማቋቋም ማህበር ክራይስትቸርች ( ኒውዚላንድ)

34. የዐማራ ማህበር በዌስተርን አውስትራሊያ

35. የአማራ አንድነት ማህበር በእስራኤል



Comments


bottom of page