በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት
- AAA-admin

- 2 hours ago
- 4 min read

ሁኔታዊ አጠቃላይ ዕይታ
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሱ ያሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ እንዳሳሳበው ይገልጻል። ይህ መግለጫ በአማራ ክልል እና አካባቢው እየተካሔደ የሚገኘውን የዘር ማጥፋት ጦርነትን እያባባሱ ያሉ አዳዲስ የመብት ጥሰቶችን ይመለከታል። በእነዚህ የመብት ጥሰቶች ውስጥ እጃቸው ያለበት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ በሚመራው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኃይሎች እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ጨምሮ አጋር የክልል ኃይሎች እና ሌሎችም ይገኙበታል። ጥቃቶቹ በዋናነት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ሲሆን የአማራ ብሔር ተወላጆችን እና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ኢ.ኦ.ተ.ቤ.) ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው።
እየታዩ ያሉ ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአስተዳደር ክልል ተከፋፍሎ ከታች ተዘርዝሯል።
የአማራ ክልል ሁኔታ
በሚያዝያ 2015 ዓ.ም.የአማራ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክልሉ ውስጥ የአገዛዙ ኃይሎች እና አጋር ታጣቂዎች የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያካትቱ ተከታታይ የጦር ወንጀሎችን እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ፈፅመዋል። የመብት ጥሰቶቹ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጭ የሚደረግ ግድያ፣ የአየር ላይ ቦምብ ጥቃት፣ አፈና እና በሴቶች ላይ የሚደረግ ወሲባዊ ጥቃትን ያካትታሉ። በተጨማሪም ጤና ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የሕዝብ ተቋማት ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን በዚህም የተነሳ የተቋማቱ ተደራሽነት ተቋርጧል።
በቅርቡ የቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ በደቡብ ጎንደር እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የሚገኙ ተጎጂዎችን አነጋግሮ በሰራው ዘገባ በክልሉ በወጣት ልጃገረዶች እና ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት በግልፅ አስቀምጧል። በዘገባው መሰረት ከ43 የጤና ተቋማት (በክልሉ ከሚገኙ ተቋማት 4 በመቶው) በተሰበሰበ መረጃ ከኀምሌ 11 ቀን 2015 እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ብቻ 2,697 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ተመዝግበዋል። እንደ ዘገባው ከተጎጂዎቹ 45 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ሲሆኑ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተጎጂዎች ኤችአይቪን ጨምሮ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ተጠቂ ሆነዋል። ዘገባው ከወጣበት ጊዜ በኋላ ጥቃቶቹ መቀጠላቸው የተገለፀ ሲሆን ለምሳሌ ኅዳር 11 የአገዛዙ ኃይሎች የግሽዓባይ ከተማ (ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰከላ ወረዳ) ተወላጅ የሆነችውን ቃልኪዳን አዲሱ የተባለች የ14 ዓመት ታዳጊ በቡድን አስገድዶ የመድፈር እና ግድያ ወንጀል ፈጽመዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በአገዛዙ ኃይሎች ድጋፍ የሚደረግላቸው የቅማንት ታጣቂዎች የዘፈቀደግ ድያ፣ አፈና እና ንብረት ማውደም ፈጽመዋል። ለምሳሌ ኅዳር 10 ታጣቂዎቹ በመተማ ወረዳ (ምዕራብ ጎንደር ዞን) ሽኩርያ ቀበሌ ውስጥ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ ሦስት ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል።
ኅዳር 11 በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ያደረጉትን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ የአገዛዙ ኃይሎች መሳሪያ ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከፍተው በርካቶች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የአገዛዙ ኃይሎች የፋኖ ታጋዮች ቤተሰብ ናቸው የተባሉትን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሰፊ አፈና እና እገታ ፈጽመዋል። ለምሳሌ ኅዳር 10 የአገዛዙ ኃይሎች በሞረትና ጅሩ ወረዳ እነዋሪ ከተማ ውስጥ ቢያንስ ሰባት ሰላማዊ ሰዎችን አፍነው ወስደዋል። አብዛኛዎቹ ታሳሪዎቹ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ አቶ ይታገሱ አቢ፣ ወይዘሮ አጥናፈወርቅ ይታገሱ፣ ወይዘሮ ሳምራዊት ይታገሱ፣ ዘርጋው ስንታየሁ፣ አቶ ወርቅ አገኝ ሽመልስ፣ ወይዘሪት ቁልጭ ሲፈታ እና ወይዘሮ አስናቀች ተጫኔ ይባላሉ።
ኅዳር 11 በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ የአገዛዙ ኃይሎች ተከታታይ ጥቃቶችን በነዋሪዎች ላይ ፈጽመው ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን የጥቃቱ ምክንያት ፋኖ አካባቢውን መቆጣጠሩን ተከትሎ የአይና ቡግና ከተማ ነዋሪዎች ከፋኖ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ክስ ነው።
በሰሜን ወሎ ዞን በአላማጣ ከተማ እና ራያ አላማጣ ወረዳ የትሕነግ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ የድብደባ፣ የማሰቃየት፣ የማስፈራራት እና የማዋከብ ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ። ታጣቂዎቹ ጥቃቶቹን የሚፈጸሙት ከተቋቋመው የትግራይ ሰፋሪ አስተዳደር እና ከመንበረ-ሰላማ የሃይማኖት ቡድን ጋር በመመተባበር ነው። ጥቃቶቹ ያነጣጠሩት በአማራ ተወላጆች፣ በጤና ባለሙያዎች እና በኢ.ኦ.ተ.ቤ. ራያ ሀገረ ስብከት አባቶች ላይ ነው። ለምሳሌ ኅዳር 1 ታጣቂዎቹ የአላማጣ ከተማ ሆስፒታል ኃላፊ የሆኑትን አቶ በላይ ሞላን አስረው በተደጋጋሚ ማስፈራራት ካደረሱባቸው በኋላ ለቀዋቸዋል። እስከ ህዳር 12 በደረሰው መረጃ መሰረት በጤና ባለሙያዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን ባለሙያዎቹ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስፈራርያ ደርሶባቸዋል። በኅዳር 5 ቀን ታጣቂዎቹ የከተማው ነዋሪዎችን እና ቢያንስ አምስት የቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባላትን አግተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ሁኔታ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሚመራው ከከተማው አስተዳደር ጋር በመተባበር በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ጥቃቶችን እና አድሏዊ አሰራሮችን ሲፈፅም ቆይቷል። ለምሳሌ በኅዳር የመጀመሪያው ሳምንት ከ1,500 በላይ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ መምህራን የብሔር ስብጥር «ለማስተካከል» በሚል ፖሊሲ ከሥራ ገበታቸው ታግደዋል።
በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ
የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ እና በኢ.ኦ.ተ.ቤ. ማኅበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ድግግሞሹ እና መጠኑ እየጨመረ መጥቷል። እነዚህ ማኅበረሰቦች በዓመታቱ ውስጥ የዘር ማጥፋት እልቂት፣ ጾታዊ ጥቃት፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እና ከፍተኛ የሆነ ጭቆና በተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች የፌዴራል ኃይሎች (ለምሳሌ የኢትዮጵያ መከላከያ)፣ የኦሮምያ ልዩ ኃይል፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና አጋር ሚሊሻዎች ገጥሟቸዋል።
ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የእነዚህ ማህበረሰብ አባላት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰውባቸዋል። በምስራቅ አርሲ ዞን በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የክልሉ ኃይሎች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀሙትን ጥቃት አጠናክረው ቀጥለዋል። ለአብነትም ኅዳር 10 በአቤ ዶንጎሮ ወረዳ በውባንቺ ቀበሌ በአካባቢው የነበረውን ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ የክልሉ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎችን አግተዋል። ከዚሁ ክስተት ጋር ተያይዞ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች ተፈናቅለዋል።
ለተጋላጭ ማህበረሰቦች የሚደረግ ጥበቃ አስፈላጊነት፣ ጉዳትን መከላከል እና አጥፊዎች እንዲጠየቁ ማድረግ
በተለያዩ ክልሎች የደረሱ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የፌደራል ኃይሎች ከክልል አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር እንደፈጸሙት ይመላከታል። በርካታዎቹ ተጎጂዎች የአማራ ብሔር ተወላጆች ሲሆኑ ታጋዮች ናቸው በሚል ስም ነው ጥቃቱ የሚያደርስባቸው። የትሕነግ ኃይሎች የሚፈጽሙትን ጥቃት በሚመለከት ጥቃቱን የሚያደርሱት የአማራ ማንነትን ከአካባቢው በማጥፋት ጤና ጣቢያዎችን፣ የእምነት ተቋማትን እና የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በትግራይ ተወላጆች ቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረገው ዘመቻ አካል እንደሆነ ይታመናል።
ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመቀስቀስ፣ እንዳልሰሙ በማለፍና በመካድ መንግስታዊ እና ወታደራዊ ባለስልጣናት፣ የመንግስት የመገናኛ ብዙኃን እና በመንግስት የተደራጁ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ትኩረት ሊደረግበት ይገባል። ለምሳሌ በቅርቡ በምስራቅ አርሲ ዞን የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተፈፀመው ጥቃት ሃይማኖት እና ብሔርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ክዶ ያወጣው መግለጫ ከፍተኛ ተቃውሞን አስተናግዷል። በየአካባቢው እየተፈጸሙ ያሉ የመብት ጥሰቶች ባሻቀቡበት በዚህ ወቅት በዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የሰብዓዊ መብት አያያዝን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዘገባ ማቅረብ አቁሟል።
ምክረ ሃሳብ
ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን፣ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ እና አጋር የክልል ታጣቂዎችን ጨምሮ በማውገዝ እንዲተባበሩ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ጥሪውን ማቅረብ ይቀጥላል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ አጋር ሀገራት እና የገንዘብ ተቋማት ለተጨማሪ ጥቃቶች የሚውሉ ወታደራዊ መሳሪያዎች ግዢ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ መስጠትን እንዲያቆሙ፤ እንዲሁም በተጨማሪም የሰብአዊ መብት ረገጣ ላይ በተሳተፉ ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ መሪዎች ላይ ያተኮረ ማዕቀብ እንዲጥሉ ማኅበሩ ጥሪውን ያቀርባል።














Comments