እየተባባሰ በመጣው የአብይ አህመድ አገዛዝ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ዘመቻ ላይ የተሰጠ መግለጫ
- AAA-admin
- 1 minute ago
- 2 min read

እየተባባሰ በመጣው የአብይ አህመድ አገዛዝ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ዘመቻ ላይ የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ከተማ በጅምላ እያካሄደ ያለውን የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ዘመቻ በጽኑ ያወግዛል። የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የመስክ መርማሪዎች በቅርብ ሳምንታት ወጣት ወንዶች እና ታዳጊዎች ላይ በድብደባ እና በዘፈቀደ እስራት በታገዘ ግዴታ ሰፊ አፈሳ እየተካሄደ እንደሆነ መዝግበዋል። ይኽ ድርጊት ሕፃናትን ለውትድርና መመልመልን የሚከለክለውን ሕግ ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያን፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት እና የሰብዓዊ መብት ህግጋቶችን የሚጥስ ነው።
ከወልድያ፣ ደብረ ታቦር፣ እብናት፣ ሸዋ ሮቢት፣ ሐይቅ፣ ባህር ዳር፣ አዲስ አበባ እና ናዝሬት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአገዛዙ ታጣቂዎች ማለትም የፌደራል ፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ አድማ ብተና እና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ሠላማዊ ዜጎችን በግዳጅ ወደ ወትድርና ለማስገባት የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል። ወጣቶች ከጎዳናዎች፣ የቡና መሸጫ ሱቆች፣ ገበያዎች እና የሐይማኖት ተቋማትን ከመሳሰሉ ሕዝባዊ ቦታዎች እየታፈኑ ይገኛሉ። በአንዳንድ ቦታዎችም መንገዶችና ሠፈሮች ተዘግተው የቤት ለቤት ፍተሻ ይካሔዳል። ማኅበራችን እንደደረሰው መረጃ በሐይቅ ከተማ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ልጆችም ጭምር እየታፈሱ በግዳጅ እንደተወሰዱ አረጋግጠናል። ልጆቻቸው እንዲፈቱ ደፍረው ለመለመን የሞከሩ ወላጆች የጦር አዛዦች እና የመንግስት ሚሊሻ መሪዎችን ጨምሮ በአካባቢው ባለስልጣናት ድብደባ ደርሶባቸዋል።
ይኽ የግዳጅ አፈሳ ሀገርን የመከላከል ተግባር አይደለም። የተስፋ መቁረጥ ድርጊት ነው። አገዛዙ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ባካሄደው የዘር ማጥፋት ጦርነት ከፍተኛ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ተማሪዎችን፣ የቀን ሰራተኞችን፣ የሐይማኖት ምሁራንን እና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጭምር በማስገደድ ለውትድርና በመመልመል ያለቁበትን ወታደሮች ለማሟላት እየጣረ ይገኛል። በአማራ ክልል እንደ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም እና ደቡብ ወሎ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶች አፈናውን በመፍራት ከቤት ንብረታቸው በገፍ እየተሰደዱ ይገኛሉ።
ጉቦ በመክፈል ከአፈሳው ለማምለጥ ያልቻሉ ሰዎች በጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ታስረው ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላት እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።
አገዛዙ እየፈጸመ ያለው በተለይም ሆን ብሎ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ላይ የሚያደርሰው አፈሳ እና ወታደሮቹን ለማሟላት የሚፈጽመው ማስገደድ፣ ማታለል እና የተለያዩ ጥቃቶች የጦር ወንጀል ነው። ይኽ ጉዳይ የአብይ አገዛዝ በሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን የሰው አልባ አውሮፕላን ድብደባ፣ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን መውደም እና የጅምላ ረሃብን ጨምሮ በሰፊው እየፈጸመ ያለው በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ነፀብራቅ ነው። ይኽንን ግፍ እየተሸከመ ያለው የአማራ ሕዝብ ነው።
አገዛዙ እየፈጸመ ባለው በእዚኽ ዘመቻ ላይ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዝምታ ገለልተኝነት ሳይሆን ተባባሪነት ነው። እነዚህን የመብት ጥሰቶች የሚያሳዩ አያሌ መረጃዎች ቢኖሩም እንደ ዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለአብይ መንግስት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እየተካሔደ ያለውን የጥፋት ጦርነት እያስቀጠሉ ይገኛሉ። የዓለም ኃያላን ዝምታ ያደፋፈረው አገዛዙ የጭካኔ ድርጊቱን በማባባስ ኢትዮጵያን ወደ መበታተንና ወደ መፈራረስ እንድትሄድ እያደረጋት ይገኛል።
የዓለም መንግስታት፣ የሚዲያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድርጊቱን እንዳላየ ማለፋቸውን እንዲያቆሙ እናሳስባለን። ዜጎችን በጅምላ በግዳጅ ለውትድርና መመልመል የመንግስት ጥንካሬ ምልክት ሳይሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውን የዘር ማጥፋት ጦርነት ለማራዘም የሚደረግ የተስፋ መቁረጥ ሙከራ ነው።
Comments