top of page
  • Writer's pictureAAA-admin

የአማራ ህዝብ ተደራዳሪ ልዑካን መሪዎችን ስለማስተዋወቅ

የተከበርከው የአማራ ህዝብ ሆይ:-


የአማራ ሕዝብ ላለፋት ሦስት አሥርት ዓመታት በአገር ምድሩ በማንነቱ ተለይቶ፣ መንግሥታዊ ውክልና ተነፍጎ፣ ከአገራዊ ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ ተሳትፎ እንዲገለል በማድረግ ተከታታይ የዘር ፍጅትና የማያባራ የማፈናቀል ጥቃት እየተፈጸመበት ቆይቷል። አማራ በማንነቱ ተደራጅቶ የተፈጸመበትን መዋቅራዊ እና ተቋማዊ ጥቃቶች መመከት ባለመቻሉ ብዙ መከራ ሲቀበል ዓመታትን አሳልፏል።


በረጅም ጊዜ የሕዝባችን ብሶት የተነሳውን ሁለገብ የአማራ ሕዝብ ንቅናቄ ለመቋቋም የተሳነው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትሕነግ) ከማዕከላዊ ስልጣን መወገዱን አምኖ ሊቀበል ባለመፍቀዱ በፈጠረው ቅራኔ፤ እንዲሁም አገራችን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና የአማራን ሕዝብ ለማንበርከክ ጦርነት ቀስቅሶ ሰፊውን ምድርህን ያካለለ ተደጋጋሚ ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ የንጹሃን እልቂት፣ መፈናቀል፣ የአካልና የመንፈስ ጉዳት፣ እንዲሁም የመሰረተ ልማትና የንብረት ውድመት አድርሶብሃል። በዚህም የተነሳ የዚህ ጦርነት ዋና ተፋላሚ እንድትሆን አስገድዶሃል። ራስህን ከወራሪው ትሕነግ ለመከላከል ተገድደህ በገባህበት ጦርነት ከፍ ያለ መስዋዕትነት የከፈልክ ቢሆንም፣ በአቤቱታ ፍትሕ ልታገኝባቸው ያልቻልካቸውን በወያኔ የሥልጣን ዘመን ወደ ትግራይ የተከለሉ የአማራ ርስቶችህን ለመቆጣጠርና የወያኔንም ግሥጋሤ ለመግታት ችለሃል።


ይህን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ሕብረት መሪነት እና በአለም አቀፉ ማሕበረሰብ አመቻችነት የሠላም ድርድር ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም የዚህ ድርድር እቅድና አካሄድ የሚታወቀውን ያህል የብልጽግና መራሹን መንግሥት እና ትሕነግ/ወያኔን እንጂ አማራውን በባለጉዳይነት ያካተተ አይደለም። ይህ ድርድር በ1983 ዓ/ም አንተ ባልተሳተፍክበት ወያኔና ኦነግ እንዳደረጉት ሥልጣን የሚቃረጡበትና እጣ ፈንታህን የሚውስኑበት መድረክ ሊሆን አይግገባም።


ባለፉት ዓመታት ለተራዘመ መከራ የዳረገህ በአማራው የአስተዳደር መዋቅር በወያኔ ምስለኔነት የተተከለው ኢሕዴን/ብአዴን/አዴፓ/የአማራ ብልጽግና የሚባለው ስብስብ እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም የአማራው ንቅናቄ እነዚህን በስምህ እየማሉ የአያት ቅድመ አያት ርስቶችህን አሳልፈው ለትሕነግ የሰጡ ቡድኖችን አስወግዶ የአማራው አስተዳደር በእውነተኛ የአማራ መሪዎች እንዲያዝ የሚያስችል ድርጅትና አመራር አልፈጠረም። በዚህ ምክንያት ብአዴን የንቅናቄውን መንፈስ ሰልቦ በስልጣን ለመቆየት የቻለ ከመሆኑም በላይ፣ ታማኝ አገልጋይነቱን ከትሕነግ ወደ ኦሕዴድ በመቀየር «ብልጽግና» ነኝ ብሎ በአማራው ላይ የሚደርሰውን መንግሥታዊ ጥቃት እንዲቀጥል አስችሎታል። ለዚህም በ«ኦሮሞ ክልል» የተፋፋመው መንግሥት መር የአማራ ጭፍጨፋ፣ በአማራ ክልል በህግ ማስከበር ስም የሚካሄደው የነቁ አማራዎችን የማሳደድ ዘመቻ፣ እንዲሁም አማራው ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ የሚጣሉበት እገዳዎች ህያው ምስክሮች ናቸው።


ብአዴን (የአማራ ብልጽግና) ሆነ ኦህዴድ (የኦሮሞ ብልጽግና) የሚመራው መንግሥት በሥልጣን ዘመናቸው በአማራው ላይ ስለፈጸሙት ወንጀል መጠየቅ ያለባቸው እንጂ የአማራውን ፍላጎት ሊያራምዱ የሚታሰቡ ወይም የአማራን ጥቅሞች እና ፍላጎቶች ወክለው መደራደር የሚችሉ አይደሉም።


የአማራውን ንቅናቄ አደራጅተው ይመራሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ድርጅቶችም ብዙ ሳይራመዱ ጥቂት መሪዎቻቸው በብልጽግና የስልጣን ዳረጎት ተሸንግለው ከዓላማቸው በማፈንገጣቸው የአማራውን እምነት ከማጣታቸውም በላይ በድርድሩ ጉዳይም አማራው ዋና ባለጉዳይ ሆኖ መቅረብ እንደሌለበት በይፋ አቋማቸውን ገልጸዋል።


በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሊካሔድ በታሰበው የሠላም ድርድር ዙሪያ ስለአማራው መወከል አስፈላጊነት ሲመካከሩ የነበሩ በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፖ፣ በአውስትራልያ እና በኒውዝላንድ የሚገኙ የአማራ ድርጅቶች (Grassroots Amhara organizations) ድርድሩን ለሚያስተባብሩት ዓለም አቀፍ አካላት በዚህ ጦርነት የአማራውን ዋና ባለጉዳይነት በማመልከት በእውነተኛ ወኪሎቹ በድርድሩ እንዲሳተፍ ካልተደረገ ድርድሩ ዘላቂ ሠላም ሊያስገኝ እንደማይችል የሚያስገነዝብ የማሳሰቢያ ደብዳቤ በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም (August-2022) ልከዋል።


ከዚህም በላይ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ(AAA) ባስተባበረው የአማራ ድርጅቶች መሪዎችና የአማራውን ፍላጎት በጥልቀት የሚረዱና በብቃት ለአማራው ፍላጎት ሊሟገቱ የሚችሉ ንቁ አማራዎች በተሳተፉበት ስብስብ የአማራ ተደራዳሪ ልዑካን ተመርጠዋል። ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘሩ አራት እንቁ ልጆችህም የልዑካኑ ቡድን መሪዎች እንዲሆኑ ተሰይመዋል፦


እነርሱም፣

1. ጀነራል ተፈራ ማሞ

2. ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

3. ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ

4. አቶ ቴዎድሮስ ትርፌ


በቀጣይም ከልዑካኑ ቡድን መሪዎች የሚቀርቡ ጥሪዎችን በንቃት በመከታተል ለጦርነቱ በግንባር እንደተሰለፍከው ሁሉ የድርድሩም ዋና ባለጉዳይ መሆንህን ለማሳወቅ ወኪሎችህን እንድትደግፍ ጥሪ እናቀርባለን።


ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም
Comments


bottom of page