top of page
 • Writer's pictureAAA-admin

የዐማራ ፋኖ ትጥቅ መፍታት እና የዐማራ ልዩ ኃይል መፍረስ የዐማራ ህዝብ የህልውና አደጋ የመጨረሻው ደረጃ ነው።

ከዓለም አቀፍ የዐማራ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ!

መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓመተ ምህረት


የአብይ አህመድ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ዐማራ ጠል አቋሙን በሰፊው በመግፋት አሁን የደረሰበት ደረጃ አይነተኛ ማሳያው የዐማራ ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት እና የዐማራ ልዩ ኃይልን ማፍረስ ነው። በተለይም የዐማራ ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት እና የዐማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስ የተነሳበትም ጊዜ፦


 • ትህነግ ከነሙሉ ትጥቁ ተጨማሪ ሠራዊት እያሰለጠነ ባለበት፣

 • ኦነጋዊያን ዐማራውን ፈጽሞ ለማጥፋት አቅደው እና ሰንደው በተነሱበት፣

 • የሱዳን የጦር ሀይል የኢትዮጵያ እና የዐማራ ክልልን ዘልቆ በወረረበት፣

 • ዐማራውን በኦሮሞ ክልል መጨፍጨፉ እና ማሳደዱ በቀጠለበት፣

 • ዐማራውን አዲስ አበባ እንዳይገባ እንዲውያም ከአዲስ አበባ ማፈናቀሉ በተፋፋመበት፣

 • ከ25 ሽህ በላይ የፋኖ፣ እና የዐማራ ህሩያን በታሰሩበት እና በታፈኑበት፣

 • ዓለም አቀፍ መንግስታት በዐማራ ህዝብ ላይ የሚካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጆሮ-ዳባ ልበስ ባሉበት እና

 • የዐማራ ህዝብ በታሪኩ ከፍተኛ የህልውና አደጋ እና አጣብቂኝ በገጠመው ወቅት ነው።


የፋኖ ትጥቅ መፍታት እና የዐማራ ክልል ልዩ ኃይል መፍረስ፣ ዐማራን ለሌላ ዙር የትህነግ ወረራ እና የኦነጋዊያን ጥቃት ያለተከላካይ አጋልጦ መስጠት ሲሆን ቀደም ሲል ትህነግ በዐማራ ህዝብ ላይ ካደረሰው ወረራ፣ ጭፍጨፋ እና መጠነ ሰፊ የተቋማት ውድመት በላይ የዐማራውን ህልውና ጨርሶ ለማጥፋት ታቅዶበት እየተፈጸመ ያለ የትህነጋዊያን እና የአብይ መራሹ ኦነጋዊያን የተቀናጀ ፀረ-ዐማራ ዘመቻ ነው። ኢትዮጵያን እና ዐማራውን ከሶስት ዙር የትህነግ ወረራ እንዲሁም አጣዬ እና ሌሎች ከተሞች በኦነግ ጦር በተደጋጋሚ ሲጠቁ ቀድሞ ደራሾቹ እና የታደጉት የፋኖ እና የዐማራ ልዩ ሀይል እንደነበሩ እየታወቀ ይህን ኃይል ትጥቁን ማስፈታት የዐማራውን ክልል ለኦነጋዊው እና ትህነጋዊው ሠራዊት የከፋ ጥቃት እንደሚያጋልጠው በጣም ግልጽ ነው።


ዐማራው አሁን ያለንበት የመጨረሻው የህልውና የትግል ደረጃ እንደሆነ ተገንዝበን በአስቸኳይ ለማይቀረው እና የመጨረሻው ትግል መነሳት አለብን። ዐማራውን ዒላማ አድርጎ በአብይ አገዛዝ የታቀደ፣ የዐማራ ግዛቶችን ለመጠቅለልና ዐማራውን ለመበታተን የታሰበ መሰሪ እቅድ እንደሆነ የዐማራ ሕዝብ ያምናል። ዐማራውን ትጥቅ የማስፈታቱ ዓላማ፣ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እና ወያኔ ፀረ-ዐማራ ኅብረታቸውን በሚያጠናክሩበት ጊዜ ማዕከላዊው መንግሥት የዐማራ አጽመርስቶችን ወልቃይትን፣ ጠለምት እና ራያን ወደ ትግራይ ክልል ለመስጠት የሸረበው ሴራ ገሀድ ወጥቷል።


በኦሮሞ ክልል ለደረሰው የዐማራ ዘር ጭፍጨፋ የአብይ አገዛዝ ዋነኛው ተጠያቂ ነው። የዐማራው የደኅንነት ዋስትናም በምንም መለኪያ በአብይ አገዛዝ ላይ ሊጣል አይችልም። ዐማራው የደህንነቴ ዋስትና ነው የሚለውን እና በራሱ ልጆች የተገነባውን የዐማራ ልዩ ኃይል የመበተን ተግባር በግልጽ የሚያሳየው የአብይ አገዛዝ እና የዐማራን ክልል የሚገዙ የአብይ ተላላኪዎች ላይ የበለጠ አለመተማመንን በመጨመር ሕዝቡ እራሱን ለመከላከል በየአካባቢው ርምጃ እንዲወስድ ያስገድደዋል። የዐማራ ልዩ ኃይል፣ የአብይ አገዛዝ ሊፈጸማቸው የሚችሉ የጭካኔ ተግባራትን ለመከላከል የሚችል አቅም ያለው እንደሆነም እናምናለን።


በሌላ በኩል መንግስት ይህን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ የሚያካሂደው ሊቃወሙኝ ይችላሉ ወይም ደግሞ ለህዝብ ድርጊቱን በማሳወቅ ተቃውሞ ያስነሱብኛል የሚላቸውን የዐማራ ምሁራንን፣ የፖለቲካ መሪዎችን እና ጋዜጠኞችን ከየሥራ ገበታቸው ላይ ያለ ህግ አግባብ እያገተ በመውሰድ እና ሰውሮ በማሰር የተለመደና የሰለቸ የሀሰት ክስ እያቀረበባቸው ባለበት ጊዜ ነው።


የአብይ አህመድ አገዛዝ ባለፉት አራት ዓመታት ባሳያቸው እጅግ ሃላፊነት የጎደላቸው ተግባራት የዐማራ ሕዝብ አገዛዙ ላይ እምነቱ ተሟጦ ያለቀ ሲሆን የዐማራ ልዩ ኃይልን ጨምሮ የክልሉ መደበኛ ፖሊስ፣ የአካባቢ ሚሊሻ እና ፋኖ የህዝባቸውን ደህንነት ለመከላከል ሲሉ ሙሉ በሙሉ እራሳቸውን ከክልሉ ትእዛዝ ውጭ በማድረግ ትጥቅ ሊያስፈታ የሚሞክር ማንኛውንም ኃይል ከመፋለም ውጭ ሌላ ምንም ዐማራጭ የላቸውም። የአብይ አገዛዝ የዐማራን ልዩ ኃይል እና ፋኖን ብቻ ለይቶ ትጥቅ ለማስፈታት የሚያደረገውን ዘመቻ ካላቆመ በዐማራ ክልልና በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ የባሰ አለመረጋጋትን መፍጠሩ የማይቀር ነው።


መላው የዐማራ ሕዝብም ራስህን ከጥፋት ለማዳን ለሕዝባዊ ትግል እንድትነሳ፣ ትግሉን በፍጥነት እንድትቀላቀል እንዲሁም አፍጥጦ የመጣውን የህልውና አደጋ በክንድህ እንድትመክት ወገናዊ ጥሪ እናቀርባለን። ይህን ፍትሃዊ ያልሆነ የአብይ መንግስት እርምጃ ለማስቆም እና በአጠቃላይ በአገዛዙ ላይ ጫና ለመፍጠር ዐማራዎች ከዚህ የሚከተሉትን ተግባራት በተቀናጀ መልክ ማድረጉ የወቅቱ ቅድሚያ ምላሽ ነው።

በዚህም መሰረት፦


1. በልዩ ሀይል እና በፋኖ ላይ የሚካሄደው የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ሁሉም ዐማራ በህዝባዊ እምቢተኝነት እንዲቃወም፣

 • የዐማራ ልዩ ኃይል ባስቸኳይ ወደ ፋኖ እንዲቀላቀል ወይም ከፋኖ ጋር እንዲቀናጅ፣ ስልታዊ እና ነጻ መሬት በመፍጥር እና ህዝቡን በማንቃት ለዐማራ ታላቅ ህዝብ ህልውና እና ለዘላለማዊ የዐማራ ክብር ተጋድሎ እንድታደርግ፣

 • የዐማራ ሕዝብ ራሱን ከዘር መጥፋት ለማዳን የሚያደርገውን ትግል የሚያፍኑ ኃይሎችን ሁሉ ይህ ተግባራቸውን ባስቸኳይ እዲያቆሙ እያስጠነቀቅን፤ ለፋኖ፣ ለልዩ ኃይል እና ለሚሊሻ አባላት ህዝባቸውን እንዲታደጉ ጥሪ እናደርጋለን፣

 • የዐማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዉ ሰፋ ያለ መንቀሳቀሻ ቦታና ከለላ እንዲያገኙ እንዲሁም የመሰረታዊ ግብአቶች አቅርቦት በገጠር ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች እና የዞን ከተሞች እንዲደረግላቸው፣

 • ዐማራው ራሱን በራሱ መጠበቅ፣ ጊዜአዊ ሕዝባዊ አስተዳደር መዘርጋት፣ መንግስታዊ መዋቅሮችን መቆጣጥር እና በየአካባቢዉ በህዝብ ቅቡል እና ታማኝ የሆኑ መሪዎችን መመደብ።

2. በዐማራ ጋዜጠኞች፣ ምሑራንና የፖለቲካ ተንታኞች ላይ የሚፈጸመው አፈና፣ እስራትና የፈጠራ ክስ እንዲቆም የታሰሩትም በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣


3. በተለያዩ የከተሞች መጋቢት 24 ቀን 2015 የተጀመረውን የህዝባዊ እምቢተኝነት ባስቸኳይ ማስቀጠል።

 • የዐማራ ህዝብ ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ በየአካባቢው በሚደረጉ የትግል እንቅስቃሴዎች፡ በማኅበራዊ መገናኛ እና በስልክ ህዝባዊ ትግሉ እንዲቀጥል በመናበብ ቅስቀሳ የማድረግ እና መረጃ በመለዋወጥ፣

 • የአብይ መንግስት ቅጥር ጀንራሎች፣ የብልጽግና ኮሚኒኬሽን እና የመንግስት መገናኛዎች የትጥቅ ማሰፈታቱ ዘመቻ በሁሉም ክልል ይካሂዳል የሚሉትን የሃስት ፕሮፖጋንዳ እንዲሆም የዐማራ ታጣቂዎች ወደ መከለከያ እና የፖሊስ ሃይል ይገባሉ የሚለውን የተለመደ የማባበያ መገለጫዎችን ማንኛውም ዐማራ ፈጽሞ እንዳይቀበል፣

 • በመላው የዐማራ ህዝብ የተቀናጀ የንግድ፣ የስራ፣ የትምህርት ማቆም አድማ በማካሄድ የሕዝባዊ ትግሉ አጋር በመሆን፣

 • ጠላቶችህ በመተባበር ለባርነት እና ጥፋት ሊዳርጉህ በርህ ላይ መቆማቸውን አውቀህ፡ ለዐማራ ህዝብ የህይወት ዋጋ ለመክፈል ከተሰለፉ ወገኖችህ ጋር እንድትቀላቀል እና ራስህንም እንድታድን በጥብቅ ስናሳስብ፡ ይህም ከዐማራ ጥፋት በፊት የመጨረሻ እድል መሆኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፣

 • የዐማራ ሕዝብ ሁሉ ይህ አፈና እስከሚቀለበስ ድረስ ቤዛ የሚሆንልህ ሌላ ሃይል እንደሌለ አውቀህ ማንኛውም መንግስታዊ ገዳይ ኃይል ወደ ዐማራ ክልል እንዳይገባ ራስህን የመከላከል የሞት ሽረት ትግል እንድታደርግ። ለዚህም ሁለንተናዊ የፈጠራ አቅምህን እንድትጠቀም።

 • የብአዴን መሪዎች ከዐማራ ህዝብ ጋር የምትቆሙበት የመጨረሻ እድላቸሁ አሁን ነው። ዛሬውኑ ከዐማራው ጎን በመቆም በተለየም የፋኖን ትጥቅ መፍታት እና የዐማራ ልዩ ኃይል መፍረስ እንድታቆሙ ወይም እንድታስቆሙ፣

 • በመላው የዐማራ ወረዳዎች ላለ የዐማራ ህዝብ፡ የወረዳ እና የዞን አመራሮች ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ፣ ይህንንም በተግባር እንድታሳዩ፣

4. በመላው ዓለም ዋና ዋና ከተሞች የተቀናጀ የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባዎችን በማካሄድ በቀጣይነት እኔም ፋኖ ነኝ፣ እኔም የዐማራ ልዩ ሀይል ነኝ በሚል መሪ ሀሳቦች ሰልፎች እንዲካሄዱ፣

5. ወደ ሀገራችን የሚላክ ገንዘብ ለአብይ አገዛዝ የሚውል ስለሆን መላው ዐማራ እንዲሁም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያ በሙሉ ገንዘብ መላክ በማቋረጥ/ በማቆም፣ የትግሉ አካል እንድትሆኑ፣
Comments


bottom of page