በሰሜን ኢትዮጵያ እየተጠናከረ ያለው የግጭት ስጋት፡ አስቸኳይ የአማራ አንድነት ግንባር አስፈላጊነት
- AAA-admin
- Jul 23
- 3 min read

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተጠናከረ ያለው የግጭት ስጋት፡ አስቸኳይ የአማራ አንድነት ግንባር አስፈላጊነት
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት እና በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ)፣ በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ እና ሌሎች ተዋናዮች መሐከል ሊፈጠር ያጠላውን የግጭት ስጋት በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል። ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በተለይም ከአራት ዓመታት በላይ የዘለቀ የማያቋርጥ የዘር ማጥፋት ጦርነት ውስጥ ለተዘፈቀው የአማራ ሕዝብ ላይ ሊያስከትለት የሚችለው መዘዝ አሳስቦናል። ወደ ግጭት የመመለስ አዝማሚያ የመነጨው የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ከመጋረጃ ጀርባ እና በፕሪቶሪያ (CoHA) ስምምነት ለትሕነግ የገባውን ቃል በአማራ ሕዝብ ትግልና ተቃውሞ ምክንያት መፈጸም አለመቻሉ እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የአማራ ባለድርሻ አካላት ከኦህዴድና ከትሕነግ የሚመጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ጠንካራ የአንድነት ግንባር ለመፍጠር እንዲረባረቡ ማኅበሩ ጥሪ ያስተላልፋል።
በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ትሕነግ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በመተባበር የአማራ እና አፋር ክልሎችን በመውረር ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ የዘር ማጥፋት፣ ስልታዊ ጾታዊ ጥቃት፣ ዘረፋ እና መሠረተ ልማቶችን ማውደም ፈጽሟል። ለምሳሌ በህዳር 2013 ዓ.ም. በማይካድራ ጭፍጨፋ ከ1,600 በላይ የአማራ ንፁሀን ዜጎች በትሕነግ ኃይሎች ተጨፍጭፈዋል፤ ይህ አሰቃቂ ክስተት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከታዩ እጅግ አሰቃቂ ግፎች አንዱ ነው።
የሰሜኑ ጦርነት የሁለት ዓመታት ውድመትን ተከትሎ የትሕነግ እና የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ በትግራይ የሚካሔደውን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶርያ የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ። የፕሪቶሪያ ስምምነት አግላይ እና ከፍተኛ ጉድለት ያለበት በመሆኑ የጦርነቱን ስፍራ ወደ አማራ ከልል ለወጠው እንጂ ጦርነትን አላስቆመም። ትሕነግ ተጠያቂ ሳይደረግ የጦር መሳሪያውን ይዞ እንዲቀጥል ተፈቅዶለታል። እንዲሁም ከኦሮሞ ብልጽግና ባገኘው ድጋፍ በራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኮረም፣ ኦፍላ፣ ዛታ፣ ጠለምት እና በአቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ ከ100,000 በላይ የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል። በእነዚህ አካባቢዎች የሰፈረው የትግራይ አስተዳደር ከፌደራል ኮማንድ ፖስት በተዘዋዋሪ ድጋፍ እየተደረገለት ከአንድ ዓመት በላይ በነዋሪዎች ላይ ሰፊ በደል ሲፈጽም ቆይቷል።
ለባለፉት ሁለት ዓመታት የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ የአገሪቷን ጦር ወደ አማራ ሕዝብ በማዞር የጦርነት ዘመቻ እያደረገ ይገኛል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ አገዛዙ የፕሪቶሪያ ስምምነት ጠባቂዎች ከሆኑት የዓለም አቀፍ አጋሮች፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የዘር ማጥፋት እልቂት፣ የሴቶችን ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም፣ የንፁሃን የጅምላ ቅጣት እና ሰው ሰራሽ ረሃብን ጨምሮ ዕለታዊ አሰቃቂ ድርጊቶችን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል። ይህንንም ተከትሎ የአማራ ፋኖ ራስን የመከላከያ ኃይል የአማራን ሕዝብ ከኦሮሞ ብልጽግና የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለመከላከል የትጥቅ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።
የትሕነግ ወቅታዊ አለማ ግልጽ ባይሆንም፣ ምናልባትም በርካታ አላማዎች እንደሚኖሩት የሚገመት ሲሆን ጦርነት ዳግም ለመጀመር ሰራዊቱን ማንቀሳቀስ ጀምሯል። የትሕነግ ኃይሎች በአማራ ክልል ወደ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች ዘልቀው መግባታቸውን ታማኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ትሕነግ የአማራ ግዛቶችን መልሶ ለመውረር እና በነባር የአማራው ተወላጆች ላይ የሚያደርጉትን የዘር ማጥፋት ለመቀጠል እንዳቀዱ አንደሚያሳይ ባለሙያዎች ያምናሉ። ትሕነግ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚ ብቻ ሳይሆን ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን በአማራ እና በሌሎች ሕዝቦች ላይ የተፈጸመ ጭቆናና ግፍን ያስቻለ የብሄር ፌደራሊዝም “አፓርታይድ” ስርዓት መሐንዲስ መሆኑ የሚታወስ ነው። ስለዚህ ትሕነግ ዳግም መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጦርነት መቀስቀሱ የጭፍጨፋ ድርጊቱን የበለጠ እንዲቀጥል የሚያስችለው ከመሆን ባለፈ ተገቢው ስራ ካልተሰራ የአማራ ሕዝብ ለአስርት ዓመታት ሲፋለም የቆየውን የዘር አፓርታይድ አገዛዝ የበለጠ ሊያጠናክረው ይችላል።
ከሁኔታዎች ውስብስብነትና ግልጽ አለመሆን አንጻር ከመቼውም ጊዜ በላይ የአማራ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የሲቪል ቡድኖች በአንድ ድምፅ መናገር እና መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ይህም የአማራን ሕዝብ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቋም ለማጠናከር እና የአማራን ሕዝብ፣ ርስት እና ማንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጠበቅ ሁሉን አቀፍ የሆነ የውስጥ ውይይት ማድረግን ይጠይቃል። የአማራ ባለድርሻ አካላት በፋኖ መሪነት የአማራን ሕዝብ ስትራተጂያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞች የማስጠበቅ፤ እየተባባሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቋቋም ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ፣ ሃብትና እርዳታ እንዲያገኝ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው ። በዚህ ወቅት አንድነት መፍጠር አለመቻል ማለት የአማራን ሕዝብ ቁልፍ ፍላጎት አለማሰጠበቅ እና የሕዝቡን የዓመታት ስቃይ ማራዘም ብቻ ሳይሆን በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት እንዲቀጥል ማስቻል ነው።
በዚህ ወሳኝ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የአማራ ባለድርሻ አካላት የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማዳንና እና የሕዝቡን ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲተባበሩ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ጥሪውን ያቀርባል። ማንኛውም የአማራ ድርጅት ወይም ቡድን ከኦሮሞ ብልጽግና ወይም ከትሕነግ ጋር የተናጥል ሽርክና በመፍጠር የአማራ ህዝብን ስትራቴጂካዊ ግቦችን ማሳካት ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ አጭር ስሌት ነው። የተጋረጠውን የዘር ማጥፋት አደጋ በተበታተነ አደረጃጀት መዋጋት በቂ አይሆንም። ይህንን በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ፣ የአማራን ሕዝብ በአንድ ሃሳብ እና የጋራ ራዕይ በመቆም ወደፊት ለማራመድ የተባበረ ግንባር ያስፈልጋል። የአንድነት ጊዜ አሁን ነው፤ ይህንን አለማድረግ መኖር የሚችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን አማራዎች ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል። የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ይህንን አንድነት ለማበረታት ከመቸውም ጊዜ በተሻለ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ያለውን አቋም እየገለፀ የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ጠንክራ ድምፅ ሁኖ የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጣል።
ሁሉም አማራ ነጻ እስካልወጣ ማንም አማራ ነጻ አይደለም።
Comments