የብልጽግና እና ስምረት በወልቃይት አማራ ህዝብ ሞት እና መፈናቀልላይ ቅቡልነትን የመፈለግ አደገኛ ጨዋታ በአስቸኳይ ሊገታ ይገባል።
- AAA-admin
- 4 hours ago
- 2 min read

የብልጽግና እና ስምረት በወልቃይት አማራ ህዝብ ሞት እና መፈናቀል ላይ ቅቡልነትን የመፈለግ አደገኛ ጨዋታ በአስቸኳይ ሊገታ ይገባል።
የአማራ ወጣት ከባሕር ዳር እስከ ደሴ፣ ከጎንደር አስከ ደብረ ብርሀን “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ”፤ “ወልቃይት አማራ ነው”፤ “ራያ አማራ ነው፤ ጠለምት አማራ ነው” የሚል መፈክር ይዘው አስከ አፍንጫው የታጠቀውን የዓጋዚ ሐይል በአደባባይ መጋፋጥ የጀመሩት የዛሬ አስር ዓመት ነበር። ከነዚህ ወጣቶች መካከል በአገዛዙ በአደባባይ ተረሽውነው መስዋዕትነት የከፈሉ በርካቶች ሲሆኑ በርካታዎቹም የዛ ወቅት የአማራ ተጋድሎ ተሳታፊዎች በመቶ ሺዎች ወደ ትግሉ አምጥተው ተጋድሏቸዉን አሁንም እንደቀጠሉ ይገኛሉ። ከአስር ዓመት በፊት በመላው አማራ የተቀጣጠለው የትግል መንፈስ በወልቃይት አና ራያ አማራዎች ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ጀግንነት የተሞላበት ትግል ሀገር አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ አድማሱን አሰፍቶ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትህነግ) አገዛዝን ከመንበረ ስልጣን አባሯል። ይህ መስዋዕትነት ቀጥሎ የአማራ ሃይሎች ባደረጉት ተጋድሎ የራያ እና የወልቃይት አማራ ህዝብ እራሱን ከትህነግ አገዛዝ እራሱን ነፃ አውጥቶ በነፃነት እራሱን ማስተዳደር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የራያ አማራ በአማራ ብልጽግና መስዋዕት አቅራቢነት በስምረት አመራሩ ጌታቸው ረዳ መሪነት በአብይ አህመድ አገዛዝ ትዕዛዝ ለትህነግ ሀይሎች ማባበያነት ለመስዋዕት ተሰጥቶ በጅምላ ግድያ እና እገታ ለከፍተኛ ስቃይ በድጋሚ ተዳርጎ ይገኛል።
ከሰሞኑ ደግሞ በብልፅግና ስልጣን ህሊናቸው የታወረ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና አመራር አባላት በተለይም የዞኑ አመራር የሆኑት ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ እና አሸተ ደምለው ከትግራይ ሰፋሪን ለመመለስ በሚል ሰበብ በራያ አማራ ላይ የተፈፀመውን በወልቃይት አማራ ላይ ለመድገም ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። ለዚሁም ፕሮጀክት ሲባል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎቹ አረጋ ከበደ፣ አሸተ ደምላው እና ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር ተሰብስበው ሚስጥር የሆነ የውሳኔ ትዛዝ እና ዝርዝር አፈፃፀም ተሰጥቷቸው የተመለሱ ሲሆን ከኦሮሞ ብልጽግና እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት (ስምረት) ፓርቲ በተሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት የትግራይ ሰፋሪዎችን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት በሚል አማራዎች መካከል ደረጃ በማውጣት ግማሹን አማራ ለአዲስ ሰፋሪዎች ቦታ ለመክፈት የምትሄዱበትን ፈልጋችሁ ሂዱ በሚል የኦሮሞ ብልጽግና አመራርን ምግባር አየደገሙ እና የአማራን ህዝብ የመንቀሳቀስ መብት የመገደብ በጅምላ የማፈናቀል እና አገር አልባ የማድረግ ወንጀል ለመፈፀም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ለዘመናት ለማንነቱ ቆራጥ ተጋድሎ በማድረግ አይበገሬነቱን ያሳየውን የወልቃይት አማራ ህዝብ ማይካድራ ጭፍጨፋን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት እንዲሁም ከ1970ዎቹ ጀምሮ ትህነግ ለፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን እና የተጎዱት አማራዎች ካሳን ጨምሮ ተገቢ ፍትህ እንዲያገኙ የሚያቀርበውን የፍትህ ጥያቄ አዳፍነን ያለምንም ተቃዋውም የአገዛዙን ትዕዛዝ እናስፈጽማለን በማለት በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ማዋከብ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ።
የአማራ ህዝብ የዘር ፍጅት እየፈፀመበት የሚገኘውን የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝን በሁሉም አቀፍ ትግል ሥልቶች መፋለም ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የአገዛዙ ምስለኔ ሹማምንት የሆኑት አረጋ ከበደ፣ አሸተ ደምላው እና ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ስለ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጉዳይ ሆነ የሰፊው አማራ ህዝብ ላይ ለመወሰን ምንም ህጋዊ መብት ወይም የሞራል መሰረት የላቸውም። ወልቃይት፣ ራያ፣ ጠለምት፣ መተክል፣ ደራ እና ሌሎችም መሰል ጥያቄዎች ያለባቸው አካባቢዎች የመሬት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የማንነት፣ የባህል፣ የታሪክና የፍትህ ጥያቄ ጉዳይ ሲሆን አጀንዳውም የአማራ ህዝብ የወል አጀንዳ እንጂ በነዚህ አካባቢ ህዝቦች ላይ የሥልጣን ሕልውናቸውን የመሰረቱ የከሰሩ ፖለቲከኞች እንደሚፈልጉት የአንድ አካባቢ ብቻ የተናጠል ጥያቄ አይደለም። ዘላቂ ምላሽ የሚያገኘውም አማራን እየጨፈጨፈ የሚገኝው የኦሮሞ ብልጽግና ከሥልጣን ተባሮ አማራው በመንግሥት መዋቅር የውሳኔ ሰጭነት ውክልና ሲኖረው ነው።
በመሆኑም የአማራ ማህበር በአሜሪካ:
፩. በኦሮሞ ብልጽግና እና በስምረት ትዕዛዝ በአረጋ ከበደ፣ አሸተ ደምላው እና ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ የተፈጸመውን ተግባር እና እየተደረገ ያለውን አማራን ከወልቃይት የማባረር ዝግጅት ሁሉም አማራ በፀኑ እንዲቃወም ጥሪውን ያቀርባል።
፪. የሕዝብ ጠበቃ የሆኑ የአካባቢ ሃይሎች ህዝብን ከዳግም ባርነት አና ጭፍጨፋ ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ያስገነዝባል።
፫. በየአካባቢው የሚፈፀምን ማንኛውም የመብት ጥሰት መረጃ በማጋራት የብልጽግና አገዛዝ ሹማምንት ለሚያደርሱት በደል በታሪክ አና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አገዛ እንድታደርጉ ይጠይቃል።










