top of page
  • Writer's pictureAAA-admin

የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትሕነግ እና የብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ የራያ አማራዎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ጥቃት ሊያወግዝ ይገባል


የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትሕነግ እና የብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ የራያ አማራዎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ጥቃት ሊያወግዝ ይገባል


የአማራ ማሕበር በአሜሪካ (AAA) ሰሞኑን ከቡድን 7 ሀገራት የወጣው የጋራ መግለጫ በኢትዮጵያ በራያ አካባቢ የተከሰተውን እና መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለውን የአማራ ተወላጆችን ለከፋ ጉዳት የዳረገውን ክስተት የሚሸፋፍን እና ሁኔታውን አሳንሶ የሚያሳይ በመሆኑ በእጅጉ ቅር ተሰኝቷል። የአማራ ማሕበር በአሜሪካ ይህ መግለጫ የገዥውን የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ (ኦህዴድ) አገዛዝን እና የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) [የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን] ያበረታታ እንደሆነ በጽኑ ያምናል።


የቡድን 7 ሀገራት የጋራ መግለጫ የወጣው የትግራይ ክልል ሃይሎች እና የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሚያዚያ 7 ቀን ጀምሮ በራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኮረም፣ ኦፍላ እና አካባቢው ያደረጉትን ወረራ ተከትሎ ሲሆን ይህም ከፍርድ ውጭ ግድያ፣ አስገድዶ መሰወር፣ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ መጠነ ሰፊ የህዝብ መፈናቀል እና የግል እና የመንግስት ንብረቶች ውድመትን ጨምሮ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙበት ነው። በሚያዚያ 11 ቀን 2016 የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (UNOCHA) ባወጣው ፍላሽ መረጃ ቁጥር 1 መሰረት ከ30,000 በላይ የራያ አላማጣ እና አካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቆቦ እና ሰቆጣ አጎራባች ከተሞች ተፈናቅለዋል። የነዚህ አካባቢዎች ነዋሪዎች አስከፊ ጉዳት ካስከተለው እና ከባድ ጭፍጨፋ ከተፈጸመበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲሁም ከጦርነቱ ከአስርት አመታት በፊት ከነበረው መጠነ ሰፊ ዘር ተኮር ጥቃቶች እና የአፓርታይድ አገዛዝ ገና ለማገገም እየታገሉ የነበሩ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል።


በንፁሀን የአማራ ተወላጆች ላይ በመላው ኢትዮጵያ እየተፈጸመ የሚገኘውን ጥቃት መግለጫው በግልጽ ያለማውገዙ እና አሻሚ የቋንቋ አገላለጽ መጠቀም መቀጠሉ የሚደርሰውን ጥፋት የሚሸፋፍን እና ጥቃቱን የሚያስቀጥል ፖሊሲ እንደሆነ ማህበሩ በፅኑ ያምናል። በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ ከተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ጋር ተያይዞ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ብተና እና መልሶ ማቋቋም (DDR) እና ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት የመመለስ ጉዳይ በተደጋጋሚ መነሳቱ፣ ይህን ሽፋን በማድረግ የአማራን ህዝብ ለመክበብ ጥቅም ላይ እየዋለ በመሆኑ ብሎም ሚሊዮኖችን ለዘር ጭፍጨፋ፣ ለዘር ማጽዳት እና ለከፋ ሰብአዊ ቀውስ አጋልጦ የሚሰጥ ስለሆነ እጅግ አሣሳቢ ነው። ይህም የተኩስ አቁም ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ያለመቻሉን በጉልህ የሚያሳይ ሲሆን ከጅምሩ ዋና ባለድርሻ የነበረውን የአማራ ህዝብ ያገለለስምምነት ስለነበረ የሽግግር ፍትህን ማስፈን ያላስቻለ እና በተግባርም COHA በኦህዴድ እና በትሕነግ መካከል “የጦርነት ስምምነት” ሆኖ ማገልገሉን ያመላክታል።


ከሰሞኑ በራያ አካባቢ በጋራ የተፈጸመው ወረራ ባሳለፍነው አመት በመላው አማራ ክልል ሲካሄድ የቆየው የዘር ማጥፋት ጦርነት ማስቀጠያ ነው። እንዳለመታደል ሆኖ፣ ቀውሱን ከመፍታትና ፍትህንና ተጠያቂነትን ከማስፈን ይልቅ የአለም አገራት መሪዎች ዝምታን እና ለአብይ አገዛዝ ይፋዊ ያልሆነ ይሁንታ መስጠትን የመረጡ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህይወት የቀጠፉ የቀደሙ ጥፋቶች ያለተጠያቂነት እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው። የአማራ ማሕበር በአሜሪካ በበኩሉ፣ አሁን በአማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ከወዲሁ ካልተገታ፣ በክልሉ የተጀመረው ጦርነት ከአገሪቱ ድንበር ውጪም ሊስፋፋ እንደሚችል ለማሳሰብ ይወዳል። ይህ ከተከሰተ ደግሞ፣ መላው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወደማያባራ የግጭት ቀጠናነት ሊሸጋገር ይችላል፣ ይህም ያልተገመተ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የሰብአዊ ቀውስ እና ዓለም አቀፍ አንድምታ ያለው የአገራት መፈረካከስ ሊያስከትል ይችላል።


ስለሆነም፣ አጠቃላይ የቀጠናውን እጣ ፈንታ ሊወስን ስለሚችል በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ እና አፋጣኝ ስልቶችን በመጠቀም ሰሞኑን በአማራው ላይ የተፈፀመውን ወረራ በግልጽ ቋንቋ ማውገዝ፣ በአስከፊ ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ቁልፍ የመንግስት እና ወታደራዊ አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣል እና በሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም መስራት በዚህ ወሳኝ ወቅት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ እርምጃዎች ናቸው።



bottom of page