መጋቢት 17 ቀን፣ 2015 (March 26, 2023)
Washington, D.C., USA
የአማራው ንቅናቄ በፀረ-አማራ አቋም ተነስተው የአገሪቱን መንግሥት የተቆጣጠሩትን ነገዳውያን፣ ነገዳዊ ሕገመንግሥታቸውን እና ክልላዊ የአስተዳደር መዋቅራቸውን አስወግዶ፣ በወራሪዎች የተነጠቀውን ለብዙ ሺ ዓመታት የኖረበትን ዐጽመ ርስቱን የማስከበርና የታሪካዊቱን ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አዘምኖ ለአማራውና ለሌላውም ዜጋ ፍትሕና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ሥርዓት የመገንባት ትግል ነው።
መግቢያ
ከሰላሳ አመታት በላይ በአማራው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ወከባ፣መሳደድ፣ መዋረድና የዘር ጥፋት ያስከተለው፣ አማራው በመሠረታት፣ በደሙና በአጥንቱ አስከብሮ ባቆያት አገሩ እንዳይኖር በነገዳዊ ህገ መንግስትና በክልላዊ የአስተዳደር መዋቅር የሚካሄድበት ጥቃት ቀጥሏል። ይህም ወያኔ እያለ ራሱን የሚጠራው የሽብር ድርጅት በ2010 ዓ.ም በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በለውጥ ስም በስልጣን ኮርቻ በተፈናጠጠው ኦነጋዊ አገዛዝ በከፋና በተጠናከረ ደረጃ ለአለፉት አምስት አመታት ቀጥሎ የአማራውን ህዝብ ህልውና እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል። ይህን ስጋትና በቀጣይ የተደቀነበትን አደጋ በመረዳት፣ የአማራው ህዝብ መውሰድ በሚገባው አጣዳፊ ራስን የመከላከልና ራስን የማዳን እርምጃ ተወያይቶ ወደ ስምምነት ለመድረስና የትግል አቅጣጫ ለመንደፍ በሰሜን አሜሪካ የአማራ ማህበራት ፌደሬሽን (ፋና) እና በካናዳ የአማራ ማኅበራት ኅብረት (ካሳ) የጠሩት በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ታላቅ ጉባዔ ከመጋቢት 16 እስከ 17 በዋሽንግተን ዲሲ ተካሂዷል። በዚሁ ጉባዔ የፋናና ካሳ መሪዎችና አባላት፣ ሌሎች በአማራ ጉዳይ የተደራጁና የሚታገሉ አካላት ምሁራንና በርካታ ቁጥር ያላቸው የአማራ ተወላጆች ተሳትፈዋል። ጉባዔው ለሁለት ቀናት፣ የአማራውን ንቅናቄ ታሪካዊ ዳራ በመቃኘት ጠላቶቹ የነዙበትን አጥፊ የሃሰት ትርክቶችና ያደረሱበትን መጠነ ስፊ ቁሳዊና ሰብዓዊ ጥቃቶች፣እንዲሁም የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በመመልከት በምሁራን በቀረቡ ጥናታዊ ሰነዶች ላይ ተወያቶ የአማራው ትግል በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃና የተጋረጡበትን የህልውና አደጋዎች በጥልቅ መርምሮ ታሪክ ያዛቡ ትርክቶችን ለማጥራት፣ የአማራውን ንቅናቄ ዓላማዎች በግልፅ ለመለየት፣ በተለይም ከፊታችን የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎችና ስልቶች የሚከተለውን መግለጫና ውሳኔ አሳልፉል።
የአማራው ንቅናቄ ታሪካዊ ዳራና በጠላቶቹ የሚነዛበት የሃሰት ትርክት አማራው፣ ኢትዮጵያን በመመሥረት በደሙና በአጥንቱ ግብር ነፃነቷን አስጠብቆ አሁን ካለችበት እንድትደርስ ያደረገ ታሪካዊ ጥንታዊና ኩሩ ህዝብ ነው። ከጥንታዊ ግሪክ ቀደምት የዓለም ፈላስፋዎች ጀምሮ እስከ መካከለኛውና እስከአለንበት ዘመን እውቅ የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች በሰፊው በጻፏቸው መጻሕፍት ይህ ሃቅ በግልፅ ሰፍሮ ይገኛል። አማራው ለኢትዮጵያ መመሥረት፣ በነጻነት መቆየትና ልማት ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ በማድረግ፣ ከሌላው ሕዝብ ጋር አብሮ በመኖር በጋብቻና በተለያዩ የኑሮ ዘርፎች በመተሳሰር ብሔራዊ አንድነቷን አጠናክሮ ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም እውቅናና ክብር ያገኘች አገር እንድትሆን አድርጓታል። በኢትዮጵያ ምስረታና የብዙ ሺ ዓመታት የነጻነት ታሪክ፣ ስለ አማራው ድርሻ እውነታው ይህ ሲሆን፣ ለአለፉት 50 ዓመታት በፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ ትርክቶች በውጭ ጠላቶችና በውስጥ አገልጋዮቻቸው የተጠነሰሰ ታሪክ የመበረዝና የማዛባት ዘመቻ ተካሂዷል። የዚህም የታሪክ ብረዛ ዋነኛ ዓላማ፣ አማራውን በጨቋኝነት፣ በተስፋፊነትና በቅኝ ገዥነት መድቦ በሌላው ህዝብ በጠላትነት እንዲታይ ማድረግ፤ በመጨረሻም ህልውናውን አደጋ ላይ በመጣል ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። በዚህም መሠረት፣ እውነቱን አዛብተው፣ የራሳቸውን ትርክት ፈጥረውበህዝብ መካከል ጥላቻና መከፋፈልን በማስፈን አማራውን ነጥሎ ለመምታትና ህልውናውን ጨርሶ ለማጥፋት የሚጥሩት [ከሁሉም መጨረሻ ኢትዮጲያን ተቀላቅለው ነገር ግን መጥተው ነባር ነገዶችን ‘መጤ ’በማለት የሚያጠፉት የኦሮሞ የወረራ ስርዓት አካሂያጆች] በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠሩት ሁሉም ነገር ይገባናል ባይ ኦነጋውያን፣ ከእነሱም በፊት ለሃያ ሰባት ዓመታት ስልጣን ይዘው ከሥልጣኔ ወደነገዳዊነት በሚመልስ ህገመንግስት’ና በክልላዊ አፓርታይድ የፖለቲካ ሥርአት አገሪቱን ከፋፍለው ለዚሁ የጥላቻና የጥፋት መሠረት የጣሉትን የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ህወሃት) ፖለቲከኞችን እውነተኛ ታሪክ መመርመር ይገባል። ከዚህ አንፃር፣ ከረዥሙ የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ጥቂት ምእት ዓመታት ወደኋላ ዘወር ብለን ስንመለከት በከፍተኛ ውድመትና ጥፋት መንሰዔነት በታሪክ የተመዘገቡ ክስተቶችን እናገኛለን።ከእነዚህም መካከል፣በተለይ አሁን ላለንበት ቀውስና ላንዣበበብን የህልውና አደጋ በተጠቃሽነት ሊቀርብ የሚችለው በ16ኛው ምእት ዓመት የተካሄደው “የጋላ ወረራ” 1 ታሪክ ነው። ይህ ክስተት፣ በበርካታ ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሃፊዎች በሰፊውተመዝግቧል።ይህ “የጋላ ወረራ”፣ በተለይም በደቡባዊ ኢትዮጵያ በምስራቅና ደቡብ ምእራብ ክፍሎች የነበሩትን ነባር ነገዶች በመጨፍለቅ፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን አጥፍቷል፤ የቀሩትንም በተለያዩ የማስገደጃ ዘዴዎች ማንነታቸውን ደምስሶና አስገድዶ በማዋሃድ በአገሪቱ የህዝብ ጥንቅር ላይ ያስከተለውን ለውጥ በአንክሮ መገንዘብ ያስፈልጋል።ይህን የታሪክ እውነታ መገንዘብ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሰፈነውን የኦነጋዊነት ርዕዮት አደገኝነት ለመረዳትና የመፍትሔ ተግባራትን ለመለየት ይጠቅማል። ኦነጋዊው አገዛዝ ይህን ሃቅ ለመሸፋፈንና በተቃራኒው ዛሬኦሮሞ የሚባለው ነገድ የተወረረ፣ መሬቱ በቅኝ የተያዘበት፣ ታሪኩ፣ ባህሉ፣ ቋንቋው እንዲጠፋ የተደረገበትና የተገፋ የሚያስመስል ታሪክን የመበረዝና የመከለስ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛል። ለዚህም፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እውቅናና ክብር ያገኘውን፣ የመላው ዓለም ጥቁር ህዝብ የነጻነት ምልክት የሆነውን የአድዋ ድል ለመካድና ለመበረዝ በቅርቡ በአገሪቱ መከላከያ ኃይል ታግዞ የፈጸመውን እጅግ አሳፋሪ እርምጃ ማስታወስ ይበቃል። አማራው በህልውናው ላይ የታወጀበትን የተቀናጀና ሁለገብ ጥቃት ለመመከት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አገር ለማፍረስ ከተቋቋሙት ከወያኔ እና ከኦነጋውያን ድርጅቶች ዓላማ ጋር ለማመሳሰል የሚደረግ ሙከራ አለ። የአማራው በአማራነቱ መደራጀትና የሚፈጸምበትን ጥቃት መቋቋም አማራጭ የሌለውና ለነገ የማይባል ተግባር ነው። የአማራው መደራጀት ለኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና የሚሰጥ እንጅ ፈጽሞ ለደህንነቷ ስጋት የሚሆን አይደለም::
አማራው በአሁኑ ወቅት ያጋጠመው የመጥፋት አደጋ በኢትዮጵያ ስልጣንን በሃይል ተቆጣጥሮ ለሃያ ሰባት ዓመታት አገሪቱን በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል ‘የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት’ እና ‘ህብረ ብሔራዊ ፈደራሊዚም’ በሚል ሽፋን የራሱን ጎሳ የበላይነት በጫነው እና በወያኔ የተመራው አገዛዝ፣ ትኩረቱ አማራውን በተለያዩ ስልቶች ማዳከምና ማጥፋት እንደነበረና ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ በኩል በርካታ እርምጃዎችን እንደወሰደ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የአማራውን ህዝብ ቁጥር በተጠና መንገድ ለማሳነስና በፖለቲካ፣ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣በባህልና በሌሎችም ዘርፎች የሚገባውን ድርሻውን እንዳያገኝ ለማድረግ፣ በቀጥታ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከመፈፀም አንስቶ የአማራው ታሪካዊ ርስት የሆኑትን እንደ ወልቃይት፣ ራያ፣ ደራ እና መተከል ያሉትን በርካታ ግዛቶቹን በትግራይና በሌሎች ክልሎች እንዲጠቃለሉ በማድረግ፣ የአማራውን ህዝብ ባህል፣ እምነቶች፣ ቋንቋ በማንቋሸሽና በማሳነስ፣ በፖለቲካና ራሱን በማስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም አገልግሎቶች በቁጥሩ ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆን፣ እንዲጎዳና ወደኋላ እንዲቀር በፖሊሲ የታገዘ ሁለገብ የዘር ማጥፋት (የጀኖሳይድ) ወንጀል ተፈፅሞበታል።
Comments