top of page
  • Writer's pictureAAA-admin

ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራው ላይ ላወጀው የዘር ማጥፋት ጦርነት የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ይቆጠቡ 



ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራው ላይ ላወጀው የዘር ማጥፋት ጦርነት የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ይቆጠቡ 


ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀው የስልክ፣ የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ኃይልን ማቋረጥን፣ ረሃብን፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ ፆታዊ ጥቃትን እና ያልታጠቁ ንጹሃን ላይ የሚካሄድ ጭፍጨፋን እንደ የጦርነት ስልት መጠቀም ከጀመሩ አስር ወራት ተቆጠሩ። የአማራ ማህበር በአሜሪካ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ከሐምሌ 29/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የደረሰውን የጉዳት መጠን እንዳጠናቀረው ከ 1,606 በላይ ንጽሃን ተገድለዋል፣ ቢያንስ 210 ሴቶች ተደፍረዋል፣ የሰብዓዊ እርዳታ በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ እንዳይደርስ ተገድቧል። እንዲሁም በክልሉ የስልክ አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጓል። የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ዋና ዋና ምዕራባውያን ኃይላት እነዚህን በክልሉ የተስፋፉ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች አውግዘዋል። 


የአብይ እግረኛ ጦር ከፍተኛ ሽንፈት እያጋጠመው በመምጣቱ ለጦርነቱ በብዛት ሰው አልባ አውሮፕላን እና የአየር ኃይሉን መጠቀም ጀምሯል። እነዚህም ጥቃቶች በብዙ ቦታዎች ላይ ንጹሃን ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ነገር ግን ይህ የስልት ለውጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመፍጠሩ የአቢይ መንግስት ተጨማሪ መሣሪያዎችንና ሌሎች ወታደራዊ ትጥቆችን ለማሟላት የውጪ እርዳታ እና ብድር ለመፈለግ ተገዷል። የካቲት 28/2016 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በተደረገው ገለፃ የዓለማቀፍ የገንዘብ ድርጅት ተወካዮች የአቢይን አገዛዝ “የኢኮኖሚ ዕድገት” እና “ተሃድሶ” በገንዘብ ለምደገፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመነጋገር በሚቀጥሉት ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የአማራ ማህበር በአሜሪካ ተረድቷል። 


የአቢይ አገዛዝ የውጭ ምንዛሬውን ለወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያውለው እየታወቀ የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት አገዛዙን በገንዘብ ለመደገፍ በማሰቡ የአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰማውን ድንጋጤና ግርምት ለመግለጽ ይወዳል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ለአቢይ አገዛዝ የገንዘብ እርዳታ ማድረግ አገዛዙ በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን የጭካኔ ተግባር ማበረታታት እንደሆነ ያምናል። ማንኛውም ያለ ጥብቅ የመቆጣጠሪያ ሁኔታ እና ያለ ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ማረጋገጫ ለኢትዮጵያ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ሁሉ እየተካሄደ ያለውን የአማራን የዘር ማጥፋት ያፋጥናል። የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዓለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችን ህግ በማክበር በዘር ማጥፋት ላይ ለተሰማሩ አካላት ሊያቀርብ ያቀደው ገንዘብ ሊያግድ ይገባዋል። ድርጅቱ ለአቢይ አገዛዝ ገንዘብ በመከልከል የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ከጥቃት ሰለባዎች ጎን መቆሙንና ማንኛውንም ዓይነት የብሄር ጥቃት፣ ማሳደድ እና ዘረኝነት እንደሚቃወም ያረጋግጣል። 


በተጭማሪም የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያለውን ተሰሚነት በመጠቀም በአዲስ አበባ ያለው አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያደርገውን ጭፍጨፋ እንዲያቆም፤ በጦርነቱ ተጠቂ ለሆኑት ሕዝቦች ጥበቃ እንዲያረጋግጥ፤ እንዲሁም በደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድ ግፊት እንዲያደርግ እንጠይቃለን። 






bottom of page