top of page
  • Writer's pictureAAA-admin

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ


ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ፡- የአለም ሃያላን ትኩረት የነፈጉት ብሎም የደገፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የአብይ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ ያወጀው የዘር ማጥፋት ጦርነት

ረቡዕ፣ የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. (ፌብሩወሪ 14, 2024)



የአማራ ማህበር በአሜሪካ (AAA) በቅርቡ ያወጣው አዲስ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ከሀምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚመራው መንግስት ሀይሎች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀውና የአብይ አህመድ መንግስት በክልሉ የሚወሰደዉ ወታደራዊ ጥቃትና ከበባ የተጠናከረዉ በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም የተቀሰቀሰውን ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ነበር። በዚህ ሪፖርት በአብይ አገዛዝ የተፈጸሙ መጠነ ሰፊ የሲቪሎች ጭፍጨፋ እና ሌሎች የጦር ወንጀል (war crime) እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል (crimes against humanity) ባህሪያትን የሚያሟሉ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተካተዋል።


የአማራ ማህበር በአሜሪካ፣ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ተከትሎ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ማለትም (ከሃምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም) የፌዴራል መንግስት፣ በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች አጋር ኃይሎች የተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ጥቃቶችን መዝግቧል።


ከጥቃቶቹም መካከል:


  • ሴቶችን፣ ህፃናትን እና አዛውንቶችን ጨምሮ ቢያንስ 1,606 ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል፤ ተጨማሪ 824 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት አድርሰዋል።

  • ቢያንስ 37 የድሮን ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን ከ333 የሚበልጡ ሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ የድሮን ጥቃቶች በዋነኝነት የገበያ ቦታዎች፣ ክሊኒኮች፣ አምቡላንሶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። የአማራ ማህበር በአሜሪካ ገና በምርመራ ላይ ያሉ ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩ የድሮን ጥቃት ሪፖርቶች ደርሰውታል።

  • ወጣት ልጃገረዶችን ጨምሮ ከ210 የሚበልጡ ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ተፈጽሟል።

  • ከመላው ኢትዮጵያ ከ10,000 የሚበልጡ የአማራ ተወላጆች በጅምላ ታስረዋል፤ የታሰሩት ደግሞ የአካላዊ ድብደባ እና ስነ ልቦናዊ ስቅይት፣ ከቤተሰብ እንዳይገናኙ ክልከላ፣ በቂ ያልሆነ ህክምና እና አስከፊ የንጽህና ሁኔታ ገጥሟቸዋል።

  • በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መረጃዎች እንዳይወጡ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎትን በተደጋጋሚ አቋርጧል፤

  • መንገደኞችን በዘፈቀደ አስገድደው ማስቆም የዘፈቀደ የፍተሻ ስራ እና አስገድዶ ጉቦ እንዲከፍሉ ማድረግ፤

  • ፋኖን ደግፋችኋል ወይም የፋኖ ሰላይ ናችሁ በሚል የሀሰት ውንጀላ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የአማራ ተወላጆችን በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከስራ ማባረር፤

  • ቢያንስ አንድ (አውራ ጎዳና) የሚባል አካባቢን በኢፌዲሪ መከላከያ እና በኦሮሚያ ክልል ኃይሎች ድጋፍ ከአማራ ክልል በመንጠቅ ወደ ኦሮሚያ ክልል ማጠቃለል እና

  • በኦሮሚያ እየተፈጸመ ካለው የዘር ማጥፋት ተርፈው በአማራ ክልል የተጠለሉ አማራዎችን ወደ ኦሮሚያ እንዲመለሱ ማስገደድ ይገኙበታል፡፡


በሪፖርቱ የተመዘገቡት ጥቃቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ የምርመራ ስራዎችን የሚያደናቅፉ ችግሮች ማለትም የኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት ገደብና መቆራረጥ እንዲሁም በቦታው ተገኝቶ ምርመራ ለማድረግ የደህንነት ስጋት ከመኖሩ አንጻር የአብይ አህመድ አገዛዝ በአማራ ህዝብ ላይ በከፈተው የዘር ማጥፋት ጦርነት በእውነታው ከደረሰው እልቂት እና ጥፋት አንጻር ጥቂት ፐርሰንቱን ብቻ የሚሸፍን መሆኑን መረዳት ይቻላል። ያም ሆኖ ሪፖርቱ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት የጦር ወንጀል (war crime) እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል (crimes against humanity) ባሕርያትን የሚያሟላ እንደሆነ እና ባለፉት አስርት አመታት በኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈጸም የቆየው የዘር ማጥፋት ወደ አማራ ክልልም ተስፋፍቶ መቀጠሉን የሚያመላክት ነው።


ይህ በንዲህ እንዳለ፣ ምዕራባውያን (western powers) እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ማውገዝ ላይ ብቻ ተወስነው የተለመደውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማካሄድ፣ ብድር በመስጠት፣ እና ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በማድረግ ለአብይ አገዛዝ እና የመከላከያ ሀይል ትብብር ማድረጋቸውን ቀጥለውበታል። ኢትዮጵያ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከ400 በላይ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ረሃብ እንዳጋጠማት ቢታወቅም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በመራዊ ከተማ አስከፊ ጭፍጨፋ ከተፈጸመበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም በጥር 19፣ 2016፣ ትልቅ ክብር የሚሰጠውን የአግሪኮላ ሽልማት (Agricola Award) ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አበርክቷል። እንደ ኤምሬትስ፣ ቱርክ፣ ቻይና እና ኢራን ያሉ ሀገራት ደግሞ በቀጥታ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጨፍጨፍ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ድሮኖችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ መንግስት መሸጣቸውን ቀጥለውበታል።


አማራዎች በተለይ ተመሳሳይ ምእራባዊያን ሃይሎች ከጥቅምት 2013 አስከ ህዳር 2015 የተካሄደውና አማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ላይ ተጽእኖ ያሳደረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አውድ በትግራይ ለተፈጸሙ ጥሰቶች በአገዛዙ ላይ ሲያሳድሩት የነበረው ጠንካራ ተፅእኖ ሲያስቡ በአሁኑ ጊዜ እነዚሁ ሀይሎች ለአብይ አገዛዝ ያላቸው ድጋፍ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ በመሆኑም ማህበራችን አለማቀፉ ማህበረስ አካሄዱን እንድያጤነውና በክልሉ ለሀገሪቷና ሰፊው የአፍሪካ ቀንድ አደጋ የደቀነው የአብይ አገዛዝ እዬደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ እንድወስድ ያሳስባል፡፡ ሆኖም በአለማቀፉ ማህበረሰብ ያለውን መዋቅራዊ ጉድለትና አይነተኛ ምላሾች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተደቀነበት አደጋ ለመቀልበስና በኢትዮጵያ እየተፈጸመበት ያለውን ዘር ማጥፋት ለአንደና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የሚያገኘው አለማቀፍ ድጋፍ ምንም ዝቅተኛ ቢሆን የአማራ ህዝብ በነጻነት እጣፈንታውን ለመወሰን አሁንም ቁርጠኛ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡





bottom of page